የፓኪስታኑ ጠ/ሚኒስትር ኢምራን ካን፤ ቢን ላደንን 'ሰማዕት' ማለታቸው ቁጣ ቀሰቀሰ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የፓኪስታኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ኢምራን ካን ኦሳማ ቢን ላንደን በአሜሪካ ተሰውቷል ማለታቸውን ተከትሎ ከተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ወቀሳ እየዘነበባቸው።
የአሜሪካውን የመስከረም 11ዱን ጥቃት ያቀነባበረው ኦሳማ ቢንላንድ በአሜሪካ ልዩ ኃይል የተገደለው በ2011 (እአአ) በፓኪስታኗ አቦታባድ ከተማ ነበር።
በወቅቱ ፓኪስታን ስለ ግድያው ተልዕኮ የምታወቀው ነገር አልነበረም።
«አሜሪካኖች እኛ ሳናውቅ መጥተው ቢን ላደንን አቦታባድ ከተማ ውስጥ መግደላቸውና አገራችንን በዓለም ፊት ማሳፈራቸውን መቼም አልረሳውም» ሲሉ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት።
ካን፤ የቢን ላደንን ሞት ለመግለጽ 'ሻሂድ፤ የተሰኘ ቃል ነው የተጠቀሙት። ቃሉ አረብኛ ሲሆን 'ሰማዕት' የሚል ትርጓሜን ይሰጣል።
የገዢው መንግሥት ተቃዋሚ የሆኑትና የቀድሞው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የሆኑት ካዋጃ አሲፍ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዴት 'ሽብርተኛን' እንዲህ ያንቆለጳጵሳሉ ሲሉ ወቅሰዋል።

የፎቶው ባለመብት, AFP
«እሱ [ቢን ላንደን] የእኔን አገር ስም አጉድፏል፤ እሳቸው [አሚር ካን] ግን ሰማዕት ሲሉ ጠርተውታል» ሲሉ ለሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ወቀሳቸውን አሰምተዋል።
ሌሎችም ታዋቂ ፖለቲከኞች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢንላደንን 'ሰማዕት' ማለታቸው አስኮርፏቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደራሴዎቻቸው ፊት ቀርበው ንግግር ያደረጉት አሜሪካ፤ ፓኪስታን አሁንም ለሽብርተኛ ቡድኖች መሸሸጊያ እየሆነች ነው ብሎ መውቀሱን ተከትሎ ነው።
የቀድሞው ታዋቂ የክሪኬት ተጫዋች ኢምራክ ካን ስለ ታሊባን ሲናገሩ ጠንከር ያሉ ቃላት አይጠቀሙም የሚል ትችት ተሰንዝሮባቸው እንደነበር አይዘነጋም።
ከአራት ዓመታት በፊት በነበራቸው የቴሌቪዥን ቃለ-ምልልስ ላይ ጠያቂው ቢን ላደን አሸባሪ ነው ይበሉ ብሎ ቢጠይቃቸውም ዳተኛ ሆነው ታይተው ነበር።












