ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በእንግሊዝ ወደ መጠጥ ቤት ጎራ የሚሉ ሰዎች መመዝገብ ሊኖርባቸው ይችላል ተባለ
እንግሊዝ ውስጥ ያሉ መጠጥ ቤቶች የደንበኞቻቸውን አድራሻ መዝግበው የመያዝ ግዴታ ሊኖርባቸው እንደሚችል የአገሪቱ ጤና ባለስልጣን ገለጹ።
የኮሮናቫይረስ ህሙማንን ለመለየት የሚደረገው ምርመራና ህሙማኑ በሽታውን ሊያስተላልፉባቸው ይችላሉ ከተባሉ ሰዎች ጋር የሚኖራቸውን ንክኪ ለይቶ ለማወቅ መጠጥ ቤቶች ደንበኞቻቸውን እንዲመዘግቡ ሊጠየቁ እንደሚችሉ የጤና ሚኒስትሩ ማት ሐንኮክ ተናግረዋል።
"ሁሉን ነገር ከመክፈታችን በፊት ስጋት አለመኖሩን ለማረጋገጥ ያስፈልጉ ብለን ካሰብናቸው ነገሮች መካከል ይህ አንዱ ነው" ሲሉ ሐንኮክ ለስካይ ኒውስ ዛሬ ተናግረዋል።
በተጨማሪም "የበሽታውን መዛመት እንደሚቀንሰው የሚታወቀውን የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብልን መጠቀምን ጨምሮ በመጠጥ ቤት ውስጥ የሚኖረው የአቀማመጥ ሁኔታን ማስተካከልም" እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
እሳቸው እንዳሉት ፊት ለፊት መቀመጥ ጀርባ ለጀርባ እና ጎን ለጎን ከመቀመጥ የበለጠ ለቫይረሱ ስርጭት አመቺ እንደሚሆን አመልክተው በመጠጥ ቤቶች ውስጥ የሚኖር የአቀማመጥ ሁኔታም ሊታሰብበት እንደሚገባ ጠቅሰዋል።
የጤና ሚኒስትሩ እንደሚሉት በሌሎች አገራት የሚገኙ መጠጥ ቤቶች፣ የምሽት ክበቦች፣ ምግብ ቤቶችና ሌሎች የአገልግሎት ቦታዎች በተመሳሳይ ደንበኞቻቸውን እንዲመዘግቡ አድርገዋል።
ከፍተኛ መጠን ያለው ምርመራን በማድረግ አድናቆትን ያገኘችው ደቡብ ኮሪያ "ከፍተኛ የተጋላጭነት" ዕድል ይኖርባቸዋል ባለቻቸው መጠጥ ቤቶች፣ የምሽት ክበቦች፣ ስፖርታዊ የማዘውተሪያ ቦታዎች፣ የሙዚቃ ዝግጅት አዳራሾችና የመሳሰሉት ቦታዎች ተጠቃሚዎች በሞባይል ስልኮቻቸው አማካይነት እንዲመዘገቡ ይደረጋል።
ነገር ግን በእንዲህ አይነቱ መንገድ የሚደረገው ምዝገባ የሰዎችን ግላዊ መረጃን ከመጠበቅ አንጻር በአንዳንድ አገራት ውስጥ ተቃውሞ ገጥሞታል።
በሰኔ ወር መጀመሪያ ላይ አንድ የቤልጂየም ሚኒስትር ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች የሚናራቸውን ንክኪ ለመለየት በሚል ቡና ቤቶችና ምግብ ቤቶች ደንበኞቻቸውን እንዲመዘግቡ ማዘዝ ሕገወጥ ነው ማለታቸውን አንድ የአገሪቱ ጋዜጣ ዘግበወል።
የእንግሊዙ ጤና ሚኒስትር ማት ሐንኮክ መጠጥ ቤቶችና መሰል ድርጅቶች ደንበኞቻቸውን እንዲመዘግቡ የማድረጉ ነገር ውድቅ ያልተደረገ መሆኑን ጠቅሰው፤ የግለሰቦች ግላዊ መረጃ ደኅንነትን በተመለከተና ሌሎች ዝርዝር የአፈጻጸም ሂደቶችን በተመለከተ ዝርዝር ያሉት ነገር የለም።