ኮሮናቫይረስ ውሸት ነው ያሉ የሩሲያ ቄስ አንድ ገዳምን ተቆጣጠሩ

አባት ሰርጌ ሮማኖቭ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አባ ሰርጌ ሮማኖቭ
ታትሟል

ኮሮናቫይረስ ውሸት ነው፣ የለም ያሉ አንድ አክራሪ የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቄስ አንድ የሴቶች ገዳምን በቁጥጥር ሥር አውለዋል።

አባት ሰርጌ ሮማኖቭ ከየካትሪንበርግ ከተማ ወጣ ብላ የምትገኝን የሴቶች ገዳም የተቆጣጠሩት ማክሰኞ ዕለት ነው።

የሰውየውን ወደ ገዳሙ መግባት ተከትሎ በርካታ መነኮሳት ገዳሙን ለመልቀቅ ተገደዋል።

አሁን የታጠቁ ፖሊሶች ለገዳሙን ጥበቃ እያደረጉለት ይገኛሉ።

አባት ሰርጌይ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳዳሪዎች እንደተናገሩት ገዳሙን ከእርሳቸው እገታ ነጻ ማውጣት የሚቻለው እርሳቸውን ጨምሮ ገዳሙን ሙሉ በሙሉ ሲያጋዩት ብቻ ነው።

እኚህ አወዛጋቢ ቄስ ባለፈው መጋቢት ከማንኛው የሰበካ አገልግሎት ታግደው ቆይተዋ።

በግንቦት ወር ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ደረጃቸውን የሚገልጸውን ትልቅ መስቀል እንዳያጠልቁ ተከልክለዋል።

የሩሲያ ቤተክርስቲያን በእርሳቸው የወደፊት እጣ ፈንታ ላይ የሚወስን አንድ ጉባኤ ጠርታ የነበረ ሲሆን እርሳቸው ላይ ስለሚወሰደው እርምጃ እየመከረ ሳለ ነው አባት ሰርጌይ ጥለው ወጥተው ገዳም የተቆጣጠሩት።

ይህ እርምጃ የተወሰደባቸው ምዕመናን ማንኛውንም በመንግሥት የሚሰጡ የማኅበረሰብ ጤና ምክሮችን ተግባራዊ እንዳያደርጉ በመስበካቸው ነው።

አባት ሰርጌይ ይህ ሐሰተኛ ያሉት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የሰይጣን ቅንብር ነው፤ የቤተክርስቲያኒቱ አስተዳዳሪዎች ከመንግሥት ሰዎች ጋር መሥራታቸውን ጌታ እየሱስ የሚወደው ተግባር አይደለም።

አባት ሰርጌይ ሰሬድኒዩራልስክ ደብሪቱን የቆረቆሯት እንደ አውሮጳዊያኑ በ2000 ሲሆን በሺህዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን የእርሳቸውን ሰበካ ለመስማት ወደዚህች ገዳም ሲጎርፉ ነበር።

በበሽታው ምክንያት የሩሲያ ባለሥልጣናት በመጋቢት 13 ሁሉኑም የእምነት ቦታዎች ዘግተው የነበረ ሲሆን ገና በዚህ ወር ነው አብያተ ክርስቲያናት እንዲከፈቱ የፈቀዱት።

አገሪቱ እስከ ትናንት ሐሙስ ድረስ ግማሽ ሚሊዮን ሰዎች በተህዋሲው ተይዘውባታል። በጠቅላላ የሟቾች ቁጥር ደግሞ 7,660 አልፏል። አንዳንድ የኅብረተሰብ ጤና አዋቂዎች ቁጥሩ ከዚህ በእጥፍ እንደሚልቅ ይገምታሉ።

በአሁኑ ሰዓት አባት ሰርጌይ የተቆጣጠሩት ገዳም በታጠቁ ፖሊሶች ከበባ ላይ ሲሆን አንድ ጋዜጠኛ ግን ሾልኮ በመግባት አግኝቷቸዋል።

"አገረ ስብከቱ እንዳልሰብክ ከለከለኝ፣ እንዳልናገር ከለከለኝ። ነገር ግን ጌታ እንድናገር ባርኮኛል" ብለውታል ወደ ውስጥ ሾልኮ ለገባው ጋዜጠኛ።

አባት ሰርጌይ ቄስ ከመሆናቸው በፊት ፖሊስ የነበሩ ሲሆን ከዚያ ወዲያ ሰው በመግደል ተጠርጥረው 13 ዓመት በእስር አሳልፈዋል። የእርሳቸው ተከታዮች ግን "አባታችን ደርጊቱን አልፈጸሙም" ይላሉ።

እኚህ ቄስ በሕጋዊ መንገድ ስማቸውን ወደ ኒኮላይ ሮማኖቭ የቀየሩ ሲሆን ይህንንም ያደረጉት ለመጨረሻው የሩሲያ ንጉሥ ዳግማዊ ኒኮላስ መታሰቢያና ክብር በሚል ነው።

ይህ ንጉሥ የተቀበረውም እርሳቸው ከቆረቆሯት ደብር በቅርብ ርቀት ላይ ነው።

እርሳቸውን ጨምሮ በርካታ ቀሳውስት በሩሲያ አዲስ የተሀድሶ እንቅስቃሴ ጀምረዋል በሚል ይተቻሉ። የቀደምት ነገሥታት አፍቃሪዎች በሚልም ይጠራል እንቅስቃሴያቸው። የአባት ሰርጌይ እንቅስቃሴም የዚህ አካል ተደርጎ ነው የሚታየው።

አባት ሰርጌይ ከዚህ ቀደም በርካታ አወዛጋቢ ስብከቶችን ያደረጉ ሲሆን ከእነዚህ ስብከቶቻቸው መካከል ፑቲንን የሚቀናቀን የኢየሱስ ጠላት በሩሲያ ይነሳል፣ አርማጌዶንም ይካሄዳል የሚለው ይገኝበታል።

ኮሮና
Banner