ነፍሰ ጡሯን በስለት ወግቶ ሰቅሏል የተባለው ተጠርጣሪ ተያዘ

ታትሟል

የደቡብ አፍሪካ ፖሊስ በተደጋጋሚ በስለት ተወግታ ዛፍ ላይ ተሰቅላ ከተገኘችው ነፍሰጡር ወጣት ጋር በተያያዘ አንድ የ31 ዓመት ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር ማዋሉን አሳወቀ።

የስምንት ወራት ነፍሰጡር የነበረችው ትሼጎፋትሶ ፑሌ በስለት ተውግታ ዛፍ ላይ ተሰቅላ መገኘቷ በደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ ድንጋጤና ሃዘን ፈጥሯል።

ተጠርጣሪው ዛሬ [ረቡዕ] ፍርድ ቤት ይቀርባል ተብሏል።

ከፑሌ መገደል በኋላ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ ከፆታዊ ጥቃት ጋር በተያያዘ ያለው ዝምታ ሊሰበር ይገባል ሲሉ ተደምጠዋል።

ፑሌ ከሰኔ 27 ጀምሮ አድራሻዋ ጠፍቶ ስትፈለግ ቆይታ ከአራት ቀናት በኋላ ነው ጆሃንስበርግ ውስጥ ከምትገኘው ሩዴፑርት መንደር ዛፍ ላይ ተሰቅላ የተገኘችው። ሬሳዋ ሲገኝ ደረቷ ላይ በርካታ ሥፍራ በስለት ተወግታ ነበር።

ፍትህ ለሼጎ (#JusticeForTshego) በሚል የማኅበራዊ ሚድያ ዘመቻ በርካታ ደቡብ አፍሪካውያን በድርጊቱ የተሰማቸውን ሃዘንና ቁጭት ገልፀዋል።

የቢቢሲዋ የጆሃንስበርግ ዘጋቢ ፑምዛ ፊህላኒ "ያለፉት ጥቂት ቀናት ደቡብ አፍሪካውያን በሃዘን የማቀቁባቸው ነበሩ" ትላለች።

ደቡብ አፍሪካ ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር እየታገለች በምትገኝበት በዚህ ወቅት ትሼጎፋትሶን የመሳሰሉ ደቡብ አፍሪካውያን ሴቶች ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት እጅግ አሳሳቢ ሆኗል።

ፆታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች አገራችንን ሃፍረት እያከናነቧት ነው ያሉት ፕሬዝደንት ራማፎሳ በሥልጣናቸው መባቻ ጥቃቱን ለማስቆም ብዙ ሞክረው ነበር።

ከእነዚህም መካከል ለፖሊሶች ተጨማሪ ሥልጠና መስጠትና ፆታዊ ጥቃትን ለሚዳኙ ፍርድ ቤቶች ተጨማሪ በጀት መመደብ ይገኙበታል።

ነገር ግን የመብት ተሟጋቾች ብዙ ይቀረናል ይላሉ፤ ሴቶች ላይ ያለን አመለካከት መቀየር ዋናው እንደሆነ በማሳሰብ።

ፕሬዝደንቱ በተለይ ደግሞ በአገሪቱ እንቅስቃሴ በተገደበበት ወቅት ሴቶች ላይ የሚደርሰው ጥቃት እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ ይናገራሉ።

"እየቀፈፈንም ቢሆንም የምናምነው ነገር ኮሮናቫይረስን ለመቀልበስ በሚል ሰዎች ቤታቸው እንዲሆኑ ሕግ ማውጣታችንን እንደ ዕድል የተጠቀሙ ወንዶች ሴቶችና ሕፃናት ላይ ጥቃት እየፀሙ ነው።''

ባለፉት ጥቂት ቀናት ብቻ ከትሼጎ ሌላ ሁለት ሴቶች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸው አይዘነጋም። ናሌዲ የተሰኘችው የ25 ዓመቷ ሴት ባለፈው ቅዳሜ ነበር በስለት የተገደለችው። ተጠርጣሪውና የፍቅር አጋሯ ነው የተባለው ግለሰብ አሁን በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ይገኛል።

ሌላኛዋ ደግሞ ሳኔሌ ምፋባ ስትሆን ሶዌቶ በተሰኘችው ከተማ አስከሬኗ ዛፍ ሥር የተገኘው ባለፈው አርብ ነው።

የፕሬዝደንቱ መግለጫ እንደሚያትተው ደቡብ አፍሪካ ውስጥ 51 በመቶ ሴቶች አጋራችን በሚሉት ሰው የተለያዩ ፆታዊ ጥቃቶች ይደርስባቸዋል።

ራማፎሳ ሕዝቡ ፆታዊ ጥቃቶችን ለፖሊስ እንዲያሳውቅ አሳስበዋል።

ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጥቃቶች በአንድ ወቅት ከተመዘገቡ በኋላ ፕሬዝደንቱ "ደቡብ አፍሪካ ለሴቶች ደኅንነት አስጊ ከሆኑ የዓለማችን ሃገራት መካከል አንዷ ናት" ማለታቸው አይዘነጋም።