በአሰሪዎቻቸው በደል ህይወታቸው አልፎ አስክሬናቸው ወደ ባህር የተወረወረው አሳ አስጋሪዎች

ታትሟል

የአንድ ወጣት ህይወት መርከብ ላይ ሳለ ካለፈች በኋላ አስክሬኑ ወደ ባህር ሲወረወር የሚያሳየው ቪዲዮ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በስፋት ከተሰራጨ በኋላ ቁጣን ቀስቅሷል። በግድያው ዙሪያም ዓለም አቀፍ ምርመራ እየተደረገ ነው።

ሟች ይሰራበት የነበረው በቻይናውያን ባለቤነት በሚተዳደረው የአሳ ማጥመጃ መርከብ ላይ በርካታ ተቀጣሪዎች እንደ ባሪያ እንደሚኖሩም ተገልጿል።

ሴፕሪ የተባለው ወጣት ከዚህ በፊት ባህር ላይ ተጉዞ የማያውቅ ሲሆን በአንድ የቻይና አሳ አጥማጅ መርከብ ውስጥ ለመስራት እድል ማግኘቱን እንደሰሙ ጓደኞቹ ይናገራሉ።

በመርከቧ ላይ ለመስራት ይከፈልሃል የተባለው የገንዘብ መጠን በጣም አጓጊ ስለነበር የ25 ዓመቱ ወጣት ከሚኖርባት ሱማትራ ደሴት ተነስቶ ለመሄድ ጊዜ አልፈጀበትም ነበር።

"ስራውን ስላገኘ በጣም እንዲሁም ቤተሰቡን ለመርዳት እድል ስላገኘ በእጅጉ ተደስቶ ነበር’’ ብላለች እህቱ ሪካ አንድሪ ፕራትማ።

ተገቢው ስልጠና እንደሚሰጠውና በየወሩ ደግሞ 400 ዶላር እንደሚከፈለው የተነገረው ሴፕሪ፤ ከሌሎች 22 ኢንዶኔዢያውያን የመርከቧ ሰራተኞች ጋር በመሆን ባሳለፍነው ዓመት የካቲት ወር ላይ ነበር ጉዞውን የጀመረው።

መርከቧ ሎንግ ዢንግ 629 ትባላለች።

ከመሄዱ በፊት ሰርቶ የሚከፍለው ገንዘብ ተበድሯት እንደነበር እህቱ ታስታውሳለች።

"ይሄን ገንዘብ የምበደርሽ ለመጨረሻ ጊዜ ነው፤ ስመለስ ብዙ ገንዘብ ይዤ እመጣለሁ፤ ቤተሰቡንም በሙሉ እረዳለሁ ነበር ያለኝ’’ ትላለች።

ነገር ግን ሴፕሪ ተመልሶ ወደ ቤተሰቦቹ አልመጣም። እህቱም ዳግም ላታየው እዛው በወጣበት ባህር ላይ ሕይወቱ አልፋለች።

ሪካ እንደምትለው ወንድሟ ባህር ላይ ሕይወቱ እንዳለፈች የሚገልጽ ደብዳቤ ደርሷታል። ከሞተ በኋላ አስክሬኑ ወደ ባህር እንደተወረወረም ተገልጾላታል።

"ወንድሜ ሞቶ ወደ ባህር መወርወሩን ስሰማ ልቤ በጣም ነበር የተሰበረው’’ ብላለች።

ሌሎች ሁለት የመርከቧ ሰራተኞች በዝችው መርከብ ውስጥ እያሉ ሕይወታቸው አልፏል። ሴፕሪ እና አንድ ሌላ ኢንዶኔዢያዊ ከአስር ወራት የባህር ጉዞ በኋላ በቀናት ልዩነት ነበር ሕይወታቸው ያለፈው።

በዚች መርከብ ውስጥ የሞቱ ሰዎች እንደ ተራ ነገር አስክሬናቸው በልብስ እየተጠቀለለ ወደ ባህር እንደሚወረወር ተነግሯል። ይህ ድርጊት ምናልባትም ማንም ሳያውቀው ሊያልፍ ይችል ነበር።

ነገር ግን አስክሬን ወደ ባህር ሲወረወር የሚያሳይ አንድ ተንቀሳቃሽ ምስል በማህበራዊ ሚዲያ መሰራጨቱን ተከትሎ ኢንዶኔዢያ ውስጥ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል።

በተጨማሪም በደቡብ ምስራቅ እስያ የተለያዩ የአሳ አጥማጅ መርከቦች ላይ የሚቀጠሩ ሰዎች የሚደርስባቸው ብዘብዛም እንደ አዲስ መነጋገሪያ ሆኗል።

"ማድረግ የምንችለው አስክሬናቸውን አጥበን ጸሎታችንን ማድረስ ብቻ ነበር’’ ብለዋል ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉና በመርከቧ ላይ የነበሩ ሌሎች ኢንዶኔዢያውያን።

ሁሉም እንደሚናገሩት ቻይናውያን አለቆቻቸው ምን እያሏቸው እንደሆነ መረዳት አይችሉም፤ ምክንያቱም ቋንቋውን አያውቁትም። በዚህም ምክንያት ግራ መጋባትና ጭንቀት ተፈጥሮባቸው ነበር።

አንድ ሌላ በመርከቧ ይሰራ የነበረ ሰው በቀን ያለእረፍት ለ18 ሰዓታት ይሰሩ እንደነበር ገልጿል።

"እነሱ (ቻይናውያን አሰሪዎች) የታሸገ ውሀ ነው የሚጠጡት፤ እኛ ግን በአግባቡ እንኳን ያልተጣራ የባህር ውሀ ነው የምንጠጣው’’ ብሏል።

የነበረው ሁኔታ በጣም አስቸጋሪና ከሚቋቋሙት በላይ ስለሆነባቸው ሴፕሪ እና ጓደኞቹ የመርከቧ ካፕቴን ጋር በመሄድ ሕክምና ለማግኘት ወደሚችሉበት ቦታ እንዲወስዳቸው ተማጽነውት ነበር። ግን አልተሳካላቸውም።

በመርከቡ ውስጥ ሴፕሪን ጨምሮ ሶስት ሰዎች ከሞቱ በኋላ አስክሬናቸውን ቀዝቃዛ ክፍል ውስጥ አቆይቶ መሬት ላይ ሲደርሱ በእስልምና ሐይማኖት ስነ-ስርዓት መሰረት እንዲቀበሩ ያቀረቡት ሀሳብም ተቀባይነት አላገኘም።

‘’ስለዚህ የነበረን አማራጭ አስክሬናቸውን አጥበን ሀይማኖታዊ ጸሎታችንን አድርሰን ወደ ባህር መወርወር ነበር።’’ ኢንዶኔዢያውን ሰራተኞቹ እንደሚሉት በመርከብ ውስጥ እያሉ ይደበደቡ እንደነበር ገልጸዋል።

በስተመጨረሻ የመርከቧ ካፒቴን ኢንዶኔዢያውያኑን ወደሌላ መርከብ ለማዘዋወር በመስማማት ሌላ መርከብ ላይ ገብተው ደቡብ ኮሪያ ሲደርሱ መሬት ለማየት በቁ።

ከመካከላቸው የአንደኛው የጤና ሁኔታ በጣም አስጊ ሁኔታ ላይ ስለነበረ ሕይወቱ መትረፍ አልቻለችም።

የስደተኞች መብት ተሟጋቾች መንግሥት ዜጎቹን ከእንደዚህ አይነት አደጋዎች መከላከል አለበት በማለት ጫና እያሳደሩ ይገኛሉ።

በመርከቧ ውስጥ የተፈጠረውን ነገር የኢንዶኔዢያ መንግሥት ኢሰብአዊ ተግባር ነው ብሎ ሲገልጸው በአገሪቱ የቻይና ኤምባሲ ደግሞ አሳዛኝ ክስተት ነው ብሎታል።

ኤምባሲው አክሎም ከኢንዶኔዢያ መንግሥት ጋር በመተባበር አጠቃላይ ምርመራ እየተደረገ እንደሆነ ስታውቋል።

በሌላ በኩል ሴፕሪ እና ጓደኞቹን የቀጠረው ድርጅት ለቤተሰቦቻቸው 13 ሺ ፓውንድ (250 ሚሊየን ሩፒያ) ካሳ ለመክፈል ቃል የገባ ሲሆን ቤተሰቦችን ግን ገንዘብ ሳይሆን ፍትህ እንፈልጋለን እያሉ ነው።