ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሬክ ማቻርና ባለቤታቸው ከኮሮናቫይረስ አገግመው ከሆስፒታል ወጡ
የደቡብ ሱዳኑ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንት ሬክ ማቻርና የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር የሆኑት ባለቤታቸው አንጌሊና ቴኒይ ከኮሮናቫይረስ ማገገማቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ።
የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ ባለስልጣናት የሆኑት ባልና ሚስት በኮቪድ-19 መያዛቸው የተነገረው ከሦስት ሳምንታት በፊት ነበር።
ሱዳን ትሪቢዩን የተቀዳሚ ምክትል ፕሬዝዳንቱን ጽህፈት ቤት ጠቅሶ እንደዘገበው ሁለቱም "ሙሉ ለሙሉ ከበሽታው አገግመው" ከሆስፒታል መውጣታቸውን አመልክቷል።
ሁለቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ከሆስፒታል እንዲወጡ የተደረገው ከበሽታው ሙሉ ለሙሉ ነጻ መሆናቸውን የሚያረጋግጠው ሁለተኛ ምርመራ ተደርጎላቸው ቫይረሱ እንደሌለባቸው ከተረጋገጠ በኋላ ነው።
ሁለቱ ጥንዶች ከሆስፒታል መውጣታቸውን ተከትሎ መደበኛ መንግሥታዊ ሥራቸውን ዛሬ ሰኞ ወደ ጽህፈት ቤታቸው በመግባት ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በደቡብ ሱዳን በርካታ የመንግሥት ባለስልጣንት በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተዘገበ ሲሆን ከመካከላቸው የተወሰኑት ደግሞ በበሽታው ሰበብ ህይወታቸው ማለፉ ተነግረወከል።
ደቡብ ሱዳን በአፍሪካ ውስጥ በግዛታቸው ውስጥ ወረርሽኙ መገኘቱን ሪፖርት ካደረጉ አገራት መካከል አንዷ ብትሆንም በየዕለቱ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች እየጨመረ መሆኑ ስለበሽታው የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።
በሌላ በኩል ደግሞ በምዕራብ አፍሪካ በምትገኘው ናይጄሪያ ውስጥ ያለችው አቢያ ግዛት ገዢ በተደረገላቸው የኮሮናቫይረስ ምርመራ በበሽታው መያዛቸው ተረጋግጦ ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ተደርጓል።
የግዛቲቱ ገዢ ኦኬዚ ኢክፒዙ በሽታው እንዳለባቸው የተረጋገጠው ከአራት ቀናት በፊት ሲሆን በህክምና ክትትል ላይ በሚቆዩበት ጊዜ ምክትላቸው ተክተዋቸው እንዲሰሩ አዘዋል።
በአቢያ ግዛት ውስጥ በኮሮናቫይረስ በሽታ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከሌሎች የናይጄሪያ ግዛቶች ጋር ሲነጻጸር ከዝቅተኞቹ ጋር የሚመደብ ሲሆን፤ የግዛቲቱ አስተዳዳሪ እንዴት ለወረርሽኙ እንደተጋለጡ የተገለጸ ነገር የለም።