አውስትራሊያውያን ለአገራቸው ቀደምት ሕዝቦች መብት ዘብ ለመቆም ሰልፍ ወጥተዋል

ታትሟል

በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ አውስትራሊያውያን 'የጥቁር ሕይወት ዋጋ አላት' እንቅስቃሴን በመቀላቀል አደባባይ ወጥተዋል።

ጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ በፖሊስ እጅ መሞቱን ተከትሎ በአሜሪካ የተቀጣጠለው ተቃውሞ አውሮፓን አልፎ አውስትራሊያ ገብቷል።

ቢሆንም አውስትራሊያውያን ሰልፍ የወጡት ለጥቁር አሜሪካውያን ብቻ ሳይሆን አቦርጅናል ለተሰኙት ቀደምት የአውስትራሊያ ሕዝቦች ጭምር ነው።

ምንም እንኳ ሲድኒ በኮቪድ-19 ምክንያት ሰዎች መሰብሰብ የለባቸውም ብላ ብትከለክልም በርካቶች የተቃውሞ መልዕክታቸውን አንግበው አደባባይ ወጥተዋል።

ሲድኒ ብቻ ሳትሆን ብሪዝበን፣ ሜልበርን፣ ሆባርት፥ አደላይድ እና ሌሎች ከተማዎችም ሰልፎች አስተናግደዋል።

ሰልፎቹ በአብዛኛው ሰላማዊና ምንም ዓይነት ነውጥ ያልተስተዋለባቸው ቢሆኑም በማዕከላዊ ሲድኒ ውጥረት እንደነበር ተስተውሏል።

አውስትራሊያውያኑ ፖሊሶች ቀደምት የአገሪቱ ሕዝቦች ላይ የሚያደርሰው በደል ይቁም ሲሉ ጩኸታቸውን አሰምተዋል። 'መተንፈስ አልቻልኩም'፤ የተሰኘው የአሜሪካው ተቃውሞ መፈክርም ታይቷል። 'ሌላ ምድር፣ ተመሳሳይ ታሪክ' የሚል መፈክር ያነገቡ በርካቶች ናቸው።

የሲድኒው ሰላማዊ ሰልፍ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት መካሄድ አይችልም ሲል አንድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አግዶ ነበር። ነገር ግን የሰልፉ አዘጋጆች ጉዳዩን ወደ ላይኛው ፍርድ ቤት ወስደው አቤት ብለው ማሸነፍ ችለዋል። ይህ የሆነው ሰልፉ ሊካሄድ 15 ደቂቃዎች ሲቀሩት ነበር።

ለሰልፉ ፈቃድ የተሰጣቸው 5 ሺህ ሰዎች ናቸው። የጤና ሚኒስቴር ግን በኮቪድ-19 ምክንያት ከ10 ሰው በላይ መሰብሰብ አይችልም ብሎ ነበር። ነገር ግን አዘጋጆቹ ሰልፈኞች ሳኒታይዘር እንዲጠቀሙና አካላዊ ርቀት እንዲጠብቁ አሳስበዋል።

ምንም እንኳ በርካቶች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አጥልቀው ቢታዩም ለአካላዊ ርቀት ቦታ እንዳልነበረ ዘገባዎች አሳይተዋል። የቪክቶሪያ ፖሊስ አካላዊ ርቀት ያልጠበቀ ሰው 1150 ዶላር ይቀጣል ቢልም ሰልፈኞቹ ስለመቀጣታቸው የተባለ ነገር የለም።

ሰልፈኞች 'ምንም ጊዜም ይህ የአቦርጅናሎች መሬት ነው' ሲሉ ጩኸታቸውን እያሰሙ ነበር።

ከ29 ዓመታት በፊት የወጣ አንድ መረጃ ቢያንስ 99 አቦርጅናሎች በፖሊስ እጅ እያሉ ሞተዋል ይላል። ጋርዲያን የተሰኘው ጋዜጣ ባደረገው ጥናት ከዚያ በኋላ ቢያንስ 432 አቦርጅኖች በፖሊስ ቁጥጥር ስር እያሉ ሞተዋል ሲል ይዘግባል።

እስካሁን በአቦርጅኖች ሞት ምክንያት አውስትራሊያ ውስጥ የተቀጣ አንድም ፖሊስ የለም።

የአውስትራሊያ ስታትስቲክስ ቢሮ እንደሚያመለክተው እስር ቤት ካሉ አውስትራሊያውያን መካከል 30 በመቶው ቀደምት ሕዝቦች ሲሆኑ ከጠቅላላው ሕዝብ ያላቸው ድርሻ ግን 3 በመቶ ነው።

በርካታ አውስትራሊያውያን ሰላማዊ ሰልፈኞች የቀደምት ሕዝቦችን ባንዲራ ለብሰው ታይተዋል።