ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በስፔን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቤት መቀመጥን በመቃወም ሰልፍ አካሄዱ
በስፔን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የአገሪቷ መንግሥት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር እየሰራ ያለውን ተግባር በመቃወም የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደዋል፡፡
የተቃውሞ ሰልፈኞቹ አካላዊ ርቀታቸውን እንዲጠብቁ ከመኪናቸው ሳይወርዱ በተለያዩ ከተሞች እንዲያሽከረክሩ 'ፋር ራይት ቮክስ' ፓርቲ ደጋፊዎቹን አሳስቧል፡፡
በመሆኑም በዋና ከተማዋ ማድሪድ ተቃዋሚዎች የስፔንን ሰንደቅ አላማ በመያዝ መኪና እያሽከረከሩ የታዩ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስተር ፔድሮ ሳንቼዝ ሥልጣናቸውን እንዲለቁ ጠይቀዋል፡፡
ስፔን በጎርጎሳውያኑ መጋቢት 14 ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ከሌሎች አውሮፓ አገራት ጥብቅ የሆኑ ውሳኔዎችን አስተላልፋለች፡፡
ይሁን እንጅ ባለፉት ሳምንታት የጣለቻቸውን ገደቦች አላልታለች፡፡ ሆኖም ማድሪድና ባርሴሎና ግን በወረርሽኙ ክፉኛ በመጠቃታቸው አሁንም ጥብቅ በሆነ የእንቅስቃሴ ገደብ ውስጥ ይገኛሉ፡፡
ነገር ግን ሁለቱ ከተሞች ከሰኞ ዕለት ጀምሮ ከቤት ውጭ መመገብንና እስከ አስር የሚደርሱ ሰዎች መሰባሰብን በመፍቀድ የጣሉትን ገደብ ማላላት ይጀምራሉ ተብሏል፡፡
ሰዎች ለምን ተቃወሙ?
አገሪቷ በጣለችው የሁለት ወራት በቤት ውስጥ የመቀመጥ ገደብ፤ ሆቴሎች፣ መጠጥ ቤቶች፣ ምግብ ቤቶች እንዲሁም የባህር ዳርቻዎችና ሌሎች የመዝናኛ ሥፍራዎች ተዘግተዋል፡፡
መንግሥት ይህን ያደረገው ወረርሽኙን ለመቆጣጠር እንደሆነ በመግለጽ በአንድ ቀን የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የፓርቲው መሪ ሳንቲያጎ አባስካል በማድሪድ ክፍት በሆነ አውቶብስ ተቃዋሚዎቹን ሲመሩ ታይተዋል፡፡
የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) አድርገው የታዩት መሪው፤ "መንግሥት ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ባከናወነው ደካማ ተግባር በቀጥታ ተጠያቂ ነው" ሲሉ ከሰዋል፡፡
በተመሳሳይ በስቪሌ፣ ባርሴሎና እና ሌሎች ከተሞችም ተቃውሞዎች ተካሂደዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስተር ሳንቼዝ ተቃውሞውን ተከትሎ ሁለት ዋና ዋና ገደቦችን እንደሚያላሉ አስታውቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የአገሪቷ ድንበሮች ለውጭ አገር ጎብኝዎች በሃምሌ ወር ጀምሮ ክፍት ይሆናሉ ብለዋል፡፡
የስፔን ላ- ሊጋ እግር ኳስ ጨዋታዎች በጎርጎሳውያኑ ሰኔ ወር መጀመሪያ እንደሚጀምሩም ተናግረዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በዩናይትድ ኪንግደም ፣ አሜሪካና ብራዚልም እምብዛም አካላዊ ርቀት ባልተጠበቀበት ቤት ውስጥ የመቀመጥ ገደቡን በመቃወም ሰልፍ መካሄዱ ይታወሳል፡፡
በኮሮናቫይረስ ክፉኛ ከተጠቁ አገራት አንዷ በሆነችው ስፔን፤ ከ28ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ የሞቱ ሲሆን 234ሺህ ሰዎች ደግሞ በቫይረሱ መያዛቸው ተነግሯል፡፡
ይሁን እንጅ በአንድ ቀን በቫይረሱ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ሲሆን ባለፉት 24 ሰዓታትም የተመዘገበው የሞት ቁጥር 56 ነው፡፡