የፓኪስታን ዓለም አቀፍ አየር መንገድ የመንገደኞች አውሮፕላን ተከሰከሰ

የፓኪስታን አየር መንገድ የመንገደኞች አውሮፕላን ተከሰከሰ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል

ከፓኪስታን ላሆር የተነሳው የፓኪስታን ዓለም አቀፍ አየር መንገድ የመንገደኞች አውሮፕላን በካራቺ መከስከሱን የአቪየሽን ባለሥልጣናት አስታወቁ፡፡

99 መንገደኞችንና ስምንት የበረራ ሰራተኞችን አሳፍሮ እንደነበር የተነገረው አውሮፕላኑ፤ ከላሆር ወደ ጂናህ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እየበረረ ነበር፡፡

አደጋው በደረሰበት በካራቺ የመኖሪያ ስፍራ ጭስ እንደሚታይ በማህበራዊ ሚዲያዎች የተጋሩ ምስሎች ያሳያሉ፡፡

የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ቤቶች ወደ ወደሙበት የአደጋው ስፍራ አቅንተዋል፡፡

የፓኪስታን አቪየሽን ባለሥልጣን ቃል አቀባይ ሳታር ኮክሃር በካራቺ "አውሮፕላን ተከስክሷል፡፡ አውሮፕላኑ ምን ያህል መንገደኞችን አሳፍሮ እንደነበር እያጣራን ነው፡፡ በእርግጥ መጀመሪያ ላይ 99 መንገደኞች እና ስምንት የበረራ ሰራተኞች ነበሩ" ብለዋል፡፡

አደጋው የተከሰተው አገሪቷ የንግድ በረራዎችን እንደገና ለመጀመር ከፈቀደች ከቀናት በኋላ ነው፡፡

በፓኪስታን ከዚህ ቀደምም በርካታ የአውሮፕላን አደጋዎች መከሰታቸው ይታወሳል፡፡

በጎርጎሮሳዊያኑ 2010 'ኤርብሉ' የተባለ የግል አየር መንገድ ንብረት የሆነ አውሮፕላን በኢስላማባድ አቅራቢያ ተከስክሶ ተሳፍረው የነበሩ 152 ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡ ይህም በፓኪስታን ታሪክ የበርካታ ሰዎች ሕይወት ያለፈበት አደጋ ነው፡፡

በ2012 በፓኪስታን 'ሆጃኤር' ንብረት የሆነ ቦይንግ 737-200 ባጋጠመው የአየር ጸባይ ለውጥ ሳቢያ ራዋልፒንዲ ለማረፍ ሲቃረብ ተከስክሶ ስድስት የበረራ ሰራተኞችና 121 መንገደኞች ሞተዋል፡፡

በ2016 እንዲሁ የፓኪስታን አየር መንገድ አውሮፕላን ከሰሜናዊ ፓኪስታን ወደ ኢስላማባድ በመብረር ላይ ሳለ በእሳት ጋይቶ ለ47 ሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት ሆኗል፡፡