ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ስፔን የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማደረግን የሚያስገድደውን ሕጓን አጠበቀች
በስፔን አካላዊ ርቀትን መጠበቅ በማይቻልበት ሁኔታ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብልን (ማስክ) በቤት ውስጥም ሆነ ከቤት ውጭ ማድረግን ግዴታ አደረገች።
በዚህ ሐሙስ ተግባራዊ መደረግ በሚጀምረው አዲሱ ሕግ የማይካተቱት ከስድስት ዓመት በታች ያሉ ሕጻናትና የጤና እክል ያለባቸው ሰዎች ብቻ ናቸው።
ምንም እንኳን በርካታ የአውሮፓ አገራት በሕዝብ መጓጓዣ አገልግሎቶች ላይ ማስክ ማድረግን አስገዳጅ ቢያደርጉም፤ የስፔን ግን ጠበቅ ያለ ሆኗል።
ስፔን በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክፉኛ ከተጠቁት የአውሮፓ አገራት አንዷ ስትሆን፤ አሁን ላይ ከቤት ያለመውጣት ገደቡን እያላላች ነው።
ቀደም ብላም በሕዝብ ማጓጓዣዎች ላይ ማስክ ማድረግን ብትጠይቅም፤ አሁን ላይ ሕጉን በአጠቃላይ በሕዝቡ ላይ ጠበቅ እያደረገች ነው።
በስፔን ከፈረንጆቹ መጋቢት ጀምሮ 28 ሺህ የሚጠጉ ሰዎች በቫይረሱ ሕይወታቸውን ሲያጡ 232 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል። ይሁን እንጂ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ነው።
በመሆኑም ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ህጻናትን ለ6 ሳምንታት ቤት ውስጥ እንዲቆዩ ማድረግን ጨምሮ በምድራችን ካሉ አገራት በጣም ጥብቅ የሆኑ እርምጃዎችን ወስዳለች።
ጠቅላይ ሚንስትር ፔድሮ ሳንቼዝ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን እንዲያራዝምላቸው ጠይቀዋል።
የተቃዋሚ ፓርቲ አባላቶች ግን የጠቅላይ ሚንስትሩን ጥያቄ ተቃውመውታል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምክር ቤቱ አዋጁን ማራዘም ሕዝቡን ከወረርሽኙ ለመታደግ ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።
ሕጉ ምን ይላል?
ሕጉ አካላዊ ርቀትን ቢያንስ በሁለት ሜትር መጠበቅ በማይቻልባቸው ጎዳናዎች ላይ፣ በመናፈሻ ቦታዎች እንዲሁም ሕዝብ በሚገለገልባቸው ቤቶች፣ በገበያ ማዕከላትና በመሳሰሉት ውስጥ የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ )ማድረግ ግዴታ መሆኑን ያትታል።
ሆኖም ከስድስት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት ይህንን እንዲተገብሩ አይገደዱም። ነገር ግን ከሦስት እስከ 5 ዓመት ያሉ ህጻናት ማስክ እንዲያደርጉ ይመከራል።
የመተንፈሻ አካል ህመም እና ሌላ የጤና እክል ያለባቸው እንዲሁም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ለማድረግ የማያስችል አካል ጉዳት ያለባቸው ሕጉን እንዲተገብሩ አይገደዱም።
ሌሎች አገራት የሚያደርጉት ምንድን ነው?
በአውሮፓ አገራት ወረርሽኙን ለመቆጣጠር የተለያዩ እርምጃዎችን ወስደዋል።
- አብዛኛው የጀርመን፣ ኦስትሪያ፣ ስሎቫኪያ እና ቼክ ሪፐብሊክ አካባቢዎች በገበያ ቦታዎችና በሕዝብ ማጓጓዣ ላይ ማስክ ማድረግን ያዛሉ።
- ስሎቫኪያ እና ቼክ ሪፐብሊክ ሕጉን በማስፋት በቢሮ ውስጥም ማስክ ማድረግን ግዴታ ነው።
- ጣሊያን አካላዊ ርቀትን መጠበቅ አስቸጋሪ በሚሆንባቸው የገበያ ቦታዎችና በሕዝብ ማጓጓዣዎች ላይ ማስክ ማድረግን ታስገድዳለች።
- ዩናይትድ ኪንግደም፣ ስዊዘርላንድ እና ቤልጂየም ማስክ ማድረግን ይመክራሉ። በስኮትላንድና በኢንግላንድ ያሉ ሰዎችም ፊታቸውን እንዲሸፍኑ ይመከራሉ።
- ግሪክ በገበያ ቦታዎች፣ በሕዝብ መጓጓዣ እና በቂ አየር በማይገባባቸው ዝግ በሆኑ ቦታዎች ላይ እንዲሁም አስጎብኝዎች ማስክ ማድረግ ግድ ነው።
የዓለም ጤና ድርጅት ጤናማ ሰዎች ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች ማስክ ማድረግ ይኑርባቸው አይኑርባቸው የሚለውን ለመወሰን በቂ መረጃ እንደሌለው ተናግሯል።