የአውስትራሊያ ፖሊስ በቢላ ጥቃት ያደረሰው ግለሰብን ተኩሶ ገደለ

ታትሟል

አንድ ግለሰብ በምዕራብ አውስትራሊያ በሚገኝ የንግድ ማዕከል ውስጥ የነበሩ ሰዎችን በቢላ በመውጋት ካቆሰለ በኋላ ከፖሊስ በተተኮሰበት ጥይት መሞቱ ተሰምቷል።

ጥቃቱ የደረሰው በምዕራብ አውስትራሊያ፤ ፒልባራ ዲስትሪክት፣ ሳውዝ ሆላንድ ከተማ በሚገኝ የንግድ ማዕከል ውስጥ ሲሆን አምስት ሰዎች ሲጎዱ የሁለቱ ጉዳት ከፍተኛ ነው ተብሏል።

የዓይን እማኞች ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን እንደተናገሩት ጩኸትና ተኩስ ከመስማታቸው በፊት ግለሰቡ "ትልቅ ቢላ" ይዞ ተገበያዩች እና ፖሊሶች ላይ ሲያወዛውዝ ነበር።

ፖሊስ በበኩሉ ለሕዝብ ደኅንነት አደጋ የነበረ ሁኔታ መከሰቱን ጠቅሶ ማንኛውም ግለሰብ የቪዲዮ ማስረጃ ካለው እንዲተባበረው ጠይቋል።

ጥቃቱ ከሽብር ጥቃት ጋር ስለመያያዙ የተባለ ነገር የለም።

አንድ ሴት ለኤቢሲ ቴሌቪዥን ስትናገር ግለሰቡ ከገበያ ማዕከሉ ውጪ እንዳየችው ገልፃ "አንዲት ጨቅላ ህጻን በጋሪ የምትገፋ ሴት ላይ ቢላውን ሲያወዛውዝ አይቸዋለሁ" ብላለች።

የፒልባራ አካባቢ ፖሊስ እንዳለው "ግለሰቡ ፖሊስ ላይ ጥቃት ለማድረስ ሲሞክር በተተኮሰበት ጥይት ህይወቱ አልፏል።"

አክሎም ጉዳቱ የደረሰባቸውን ሰዎች በተመለከተ ምርመራ እያደረገ መሆኑን አስታውቋል። የሟቹ ማንነት እስካሁን ድረስ አልተገለፀም።

ሳውዝ ሆላንድ በምዕራብ አውስትራሊያ ፒልባራ አካባቢ የምትገኝ ትንሽ ከተማ ስትሆን በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎች በማዕድን ማውጣትና በኢንደስትሪዎች ላየይ ተቀጥረው የሚሰሩ ናቸው።