ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ ቶም ሃንክስ ለስምንት አመቱ አውስትራሊያዊ ደብዳቤ በመጻፍ ስጦታ ላከ
ቶም ሃንክስ ለአውስትራሊያዊው ታዳጊው ኮሮና፣ በስሙ የተቀረፀ መተየቢያ እና የእጅ ጽሁፍ የሰፈረበት ደብዳቤ ላከ።
ኮሮና ዲ ቭራይስ ስምንት አመቱ ነው። ለቶም ሃንክስና ባለቤቱ መጀመሪያ ደብዳቤ የጻፈው በኮሮና ታመው ክዊንስላንድ ተቀምጠው በነበረበት ወቅት ነው።
ለልጃቸው ኮሮና ሲሉ ስም የሰጡ ቤተሰቦችም ሆኑ ልጁ ስሙ እንዲህ ከሩቅ የሚሸሽ ቫይረስ፣ በሳይንስም ሆነ በሃይማኖት ለማጥፋት ቀን ተሌት የሚተጋ ወረርሽኝ መሆኑን አያውቁም ነበር።
"አንተና ባለቤትህ የኮሮናቫይረስ መያዛችሁን ከዜና ላይ ሰማሁ" ካለ በኋላ " አሁን ጤንነታችሁ አንዴት ነው?" ሲል ደብዳቤ የጻፈው ቶም ሃንክስና ባለቤቱ በኮቪድ-19 መያዛቸውን ከገለፁ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ነው።
አክሎም ስሙን እንኳ ቢወደውም ትምህርት ቤት ግን ጓደኞቹ "ኮሮናቫይረስ" እንደሚሉት ገልጿል።
" ሰዎች እንደዚህ ብለው ሲጠሩኝ አዝናለሁ፤ እናደዳለሁ" ብሏል።
በምላሹም ቶም ሃንክስ "ውድ ወዳጄ ኮሮና" ሲል ምላሹን ሰጥቷል።
"ደብዳቤህ እኔና ባለቤቴን ጥሩ ስሜት እንዲሰማን አድርጓል። መልካም ወዳጃችን በመሆንህ አናመሰግናለን። መልካም ጓደኛ፣ ጓደኞቹ በከፋቸው ወቅት ጥሩ ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጋል"
ቶም ሃንክስና ባለቤቱ በአውስትራሊያ ለሶስት ሳምንት ከኮሮናቫይረስ ካገገሙ በኋላ ወደ አሜሪካ ተመልሰዋል።
የኦስካር አሸናፊው ተዋናይና ፕሮዲውሰር ቶም ለታዳጊው " ኮሮና የሚል ስም ያለው ታዳጊ የማውቀው አንተን ብቻ ነው-ልክ በፀሀይ ዙሪያ እንዳለው ቀለበት-ዘውድ" ሲል አጽናንቶታል።
ቶም ሃንክስ በለይቶ ማቆያ ውስጥ ባለበት ወቅት ይጠቀምበት የነበረውን መተየቢያ ማሽን በኮሮና ስም አስቀርጾ ልኮለታል።
"ይህ መተየቢያ ማሽን ይስማማሀል ብዬ አስባለሁ" ካለ በኋላ "አውስትራሊያ ጎልድ ኮስት ባለሁ ሰአት አብሮኝ ነበር፤ አሁን ደግሞ ወደ አንተ መጥቷል፤ ትልልቅ ሰዎችን እንዴት እንደሚሰራ ጠይቃቸው እና መልሰህ በዚሁ ማሽን ጻፍልኝ"
የታዳጊው ዲ ቭራይስ ቤተሰቦች ለአውስትራሊያ መገናኛ ብዙኀን እንደተናገሩት ኮሮና ለቶም ሃንክስ ደብዳቤ እንዲጽፍ ያሳመኑት እነርሱ መሆናቸውን ገልፀው ልጁም "አዲስ ጓደኛ በአሜሪካ" በማግኘቱ ደስተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
ኮሮና ሃንክስን የሚያውቀው በቶይ ስቶሪ ፊልሞች ላይ ውዲን ሆኖ ሲተውን ነው።
ሃንክስ በደብዳቤው መጨረሻ ላይ በራሱ እጅ ጽሑፍ የዝነኛውን ፊልም ማጀቢያ ሙዚቃ በሚጠቅስ መልኩ "PS! You got a friend in ME!" ሲል አስፍሯል።
ባለፈው ወር ቶም ሃንክስና ባለቤቱ ወደ አውስትራሊያ ለሥራ ተጉዘው በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን አሳውቀው ነበር።