ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስና ስቅለት፡ አፍሪካዊያን በምን ሁኔታ በዓሉን እያከበሩት ነው?
በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ስፍራ ከሚሰጣቸው አበይት በዓላት መካከል የእየሱስ ክርስቶስ ልደት፣ ስቅለትና ትንሳኤ ዋነኞቹ ናቸው።
የጎርጎሳውያን የዘመን አቆጣጠርን በሚከተሉ የክርስትና አማኞች ዘንድ ዛሬ ስቅለት (ጉድ ፍራይደይ) ተብሎ የሚጠራው ዕለት ነው።
ነገር ግን እንድ ድሮው ስቅለትንም ይሁን በመጪው እሁድ የሚከበረውን የትንሳኤ በዓልን ለማክበር ምንም አይነት ሽር ጉድ አይታይም።
ዓለም እንዲሁም አህጉረ አፍሪካ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ስርጭት ለመግታት ትንቅንቅ በገባችበት ወቅት ለሰዎች ዋናው ጉዳይ በሕይወት መቆየት ሆኗል።
በትላልቅ የድምጽ ማጉያዎች ይሰብኩ የነበሩ አብያተ ክርስቲያናትና አገልግሎትንም ሆነ ቡራኬን ለማግኘት ይጋፉባቸው የነበሩ የአምልኮ ቦታዎች ወና ከሆኑ ሰነባብተዋል።
ከፍ ባለ ድምጽ መዝሙርም ሆነ ስብከት አይሰማም፤ አብያተ ክርስቲያናት በምዕመኖቻቸው መካከል ወረርሽኙ እንዳይስፋፋ በሚል ጥንቃቄ በሮቻቸውን ከርችመዋል።
ሆኖም ምስጋና ለቴክኖሎጂ ይግባውና የተወሰነም ቢሆን ሕዝቡ የበዓሉ ስሜት እንዲሰማውም ሆነ አገልግሎቶቹንም እንዲያገኝ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች፣ እንዲሁም በቴሌቪዥን ጣቢያዎች በመተላለፍ ላይ ናቸው።
የቅርብ ሩቅ እንዲሉ ሁሉም በቤቱ ተቀምጦ ትናንትን እየናፈቀ፣ ነገን በተስፋ እያለመም አገልግሎቱን መካፈል አማራጭ የሌለው ሆኗል።
በማያቋርጥ ለውጥ ውስጥ ሆና እንዲህ አይነት የትንሳኤ በዓል አከባበር አይታ በማታውቀው ዓለም ይህንን መቀበልም ግዴታ ሆኗል። ብዙ ክርስቲያኖችም ይህችን እለት በቤታቸው ውስጥ ሆነው እያሳለፏት ይገኛሉ።
ስቅለቱን ብቻ ሳይሆን ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር የሚደረገውንም ትግል አብሮ በማሰብ በተቀላቀለ ስሜት በማክበር ላይ ናቸው።
የተለያዩ አገራትም በዓለም ጤና ድርጅት ትዕዛዝ መሰረት የሕዝቦቻቸውን እንቅስቃሴ መገደብ፣ በቫይረሱ የታመሙ ሰዎች ጋር ንክኪ አላቸው ተብለው የሚጠረጠሩትን መለየት፣ ለይቶ ማቆየት እንዲሁም ምርመራ የማድረግ ሥራዎችን ማከናወን ዋና ትኩረታቸው ሆኗል ።
ከአፍሪካ የበሽታዎች ቁጥጥርና ክትትል በተገኘው መረጃ 12 ሺህ የሚሆኑ ሰዎች በአህጉሪቱ ውስጥ በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።
በአፈረካ ውስጥ ባሉ ሃምሳ ሁለት አገራት ውስጥ ቫይረሱ መኖሩ የተረጋገጠ ሲሆን 630 ሰዎችም ህይወታቸውን አጥተዋል። ከ1500 በላይ ሰዎችም አገግመዋል።
በርካታ የአፍሪካ አገራት ቤት የመቀመጥ ውሳኔዎችን ያስተላለፉ ሲሆን ደቡብ አፍሪካ ለሁለት ሳምንት አሳልፋው የነበረውን ውሳኔ ለሌላ ሁለት ሳምንት ስታራዝም ፣ ጋናም እንዲሁ ለተጨማሪ አንድ ሳምንት ይቀጥል ብላለች።
በናይጄሪያና በካሜሮን በሚገኙ አንዳንድ ከተሞች የጤና ባለሙያዎች ቤት ለቤት እየዞሩ ከኮሮናቫይረስ ህመምተኛ ጋር ንክኪ ያላቸውን ሰዎች የመለየት ሥራ እንዲሁም ምልክቱ ያለባቸው ሰዎችን ወደ ጤና ማዕከላት ለመውሰድ እየሰሩ ነው።
ላይቤሪያም በዛሬው እለት ቤት የመቀመጥ አስገዳጅ ውሳኔን አሳልፋለች፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ለአምስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን አፅድቋል።