ኮቪድ-19 የሐብታም በሽታ ነው ብለው የሚያምኑት የብራዚል ድሆች

የአካባቢው ነዋሪዎች ተራርቀው በመቆም ስልጠና ላይ ሲሳተፉ
የምስሉ መግለጫ, የአካባቢው ነዋሪዎች ተራርቀው በመቆም ስልጠና ላይ ሲሳተፉ
ታትሟል

ሌላ ቦታ ሕይወት ተቀዛቅዛ ይሆናል፤ በሳኦ ፖሎ ጭርንቁስ ሰፈሮች ግን ያው ናት፤ ትሾራለች።

ሞተረኞች ዕቃና ሰው ያመላልሳሉ፣ ለፍቶ አዳሪዎች ወደ ሥራ ተፍ ተፍ ይላሉ፣ ሌቦችም ወደ ኪስ ይዘልቃሉ። እርግጥ ነው ጥቂት ሱቆች አልተዘጉም አይባልም…።

"ሰው ገቢው ከእጅ ወደ አፍ ሲሆን እንዴት ነው ሳትሰራ ቤት ዋል የሚባለው?" ይላሉ የዚያ ሰፈር ነዋሪዎች። በረሃብ ከመሞት በኮሮናፃይረስ መሞት…በስንት ጣዕሙ ይላሉ።

በዚህ ብራዚሎች ፋቬላ በሚሏቸው ጭርንቁስ ሰፈሮች ኮቪድ-19 አስፈሪ አይደለም። እንዲያው ብዙ ሰው ወረርሽኙን የሃብታሞች በሽታ አድርጎ ነው የሚያየው።

አሁን አሁን ነው ከውጭ የመጣው በሽታ ድሀንም ሊተናኮል እንደሚችል እየተረዱ ሲመጡ ፍርሃት ሽው ያለባቸው።

የብራዚል ፋቬላዎች ሰው ከሰው ተዛዝሎ፤ ቤት ከቤት ተቃቅፎ፣ ጣሪያ በንፋስ በርሮ እንዳይጠፋ ድንጋይ ተጭኖበት የሚኖርበት የምንዱባን መንደር ነው።

የጎዳና ፕሬዝዳንቶችና የብራዚሉ ፕሬዝዳንት

ጊልሰን ድምጽ ማጉያውን ይዞ በዚህ ሰፈር ኳስ መጫወቻ ሜዳ ቆሟል። የሰፈሩ አለቃ ነው። ፕሬዝዳንታችን እያሉ ነው የሚጠሩት ነዋሪዎች። በጭርንቁስ ሰፈሮች "የጎዳና ፕሬዝዳንቶች" አሉ።

አሁን ጊልሰን እያደረገ ያለው የሰፈሩ ሰዎች በተቻለ መጠን ስለንጽሕና እንዲያስቡ ነው። ቢችሉ ቢችሉ ደግሞ ከቤት እንዳይወጡ…

ይህ ግን በቀላሉ የሚሳካ አይደለም።

መካከለኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ቤታቸው ቁጭ ብለው በኮምፒውተር ሁሉን እየሰሩ የሚያሳስባቸው በቂ ሳኒታይዘር አለ ወይ የሚል ነው። በዚህ ሰፈር ግን ይህ መንደላቀቅ ነው።

"እጅ ማጽጃ አልኮል 5 ዶላር ነው። ከየት ይመጣል 5 ዶላር" ይላል ጊልሰን።

ጊልሰን
የምስሉ መግለጫ, ጊልሰን

ጊልሰን አሁን እያደረገ ያለው ድሆችን በተቻለ መጠን ከዚህ በሽታ መታደግ ነው እንዳይዘናጉ ማንቃት…

"ስለቫይረሱ የተነገሩት ብዙዎቹ ነገሮች ለእኛ ሰፈር የሚሆኑ አይደሉም" ይላል። ስለዚህ ብዙዎቹን መመሪያዎች ለሰፈሩ በሚስማማ መልኩ ማስተዋወቅ አለበት።

ለምሳሌ አትጠጋጉ የሚለው ለዚህ ሰፈር አይሰራም። ተጠጋግቶ ነዋ ሕዝቡ የሚኖረው። ወዴት ሂድ ትለዋለህ?

ሺ ሕዝብ አብሮ ነው ተዘዝሎ እየኖረ ያለው!

ያም ሆኖ ጊልሰን የሰፈሩ ሰዎች በተቻለ መጠን ርቀትን መጠበቅ እንዲያውቁ ይሞክራል።

ከበጎ ፈቃደኞች ሌላዋ ፍላቪያ ሲልቫ ናት።

"እኔን የሚያስጨንቀኝ በሽታው እዚህ ሰተት ብሎ ገብቶ እንዳይጨርሰን ነው" ትላለች። ከሁሉ ከሁሉ ነዋሪዎች ወረርሽኙን የምር አድርገው አለመውሰዳቸው ያስጨንቃታል።

የብራዚሉ ፕሬዝዳንት "ይዘላብዳሉ"

በዚህ የሳኦ ፖሎ ጭርንቁስ ሰፈር ሴቶች ተሰብስበው አፍ ለአፍ ገጥመው ሲያወሩ ከጎዳና ፕሬዝዳንቶች አንዱ መጥቶ "ተበተኑ" ይላቸዋል። ለምን ብለው ሲጠይቁ ኮሮናቫይረስ ይተላለፍባችኋል ይላቸዋል። ሳቃቸውን ለቀቁት።

ይህ የሁልጊዜ ኩነት ሆኗል በብራዚል የድሀ ሰፈሮች። ለዚህ አንዱ ምክንያት ድህነት ሲሆን ሌላኛው ግን የብራዚሉ ፕሬዝዳንት ጄር ቦልሶናሮ ናቸው።

ጊልሰን እንደሚለው ኮሮናን ከመከላከል ባልተናነሰ ሌላው እየተከላከልነው ያለው ቫይረስ የፕሬዝዳንት ቦልሶናሮን መዘላበድ ነው ይላል።

ፕሬዝዳንቱ ኮቪድ-16ን ጉንፋን አስመስለው ነው የሚናገሩት። ዜጎች ሥራ እንዲሰሩ እንጂ ቤት እንዲውሉ አይፈልጉም።

በስንት መከራ ቤት እንዲውሉ ያደረግናቸው ሰዎች ቦልሶናሮ በቲቪ ቀርቦ ሲዘባርቅ ይሰሙና ወደ ሥራ ይመለሳሉ ይላል ጊልሰን።

በጊልሰን እምነት ፕሬዝዳንት ቦልሶናሮ በብራዚል በኮሮና ለሚጠፋ እያንዳንዱ ነፍስ ተጠያቂ ናቸው። በዚያ ላይ እርሳቸው በጭርንቁስ ሰፈር የሚኖረውን 13 ሚሊዮን ብራዚላዊ ረስተውታል። ትዝም አይላቸው።

ስለዚህ ነዋሪዎች ነገሮችን በራሳቸው ለመያዝ ይተጋሉ። ለምሳሌ የአካባቢው በጎ ፈቃደኞች ሁለት አምቡላንስ ተከራይተው እዚያው ኳስ ሜዳ አጠገብ ሸራ አልብሰውታል። ጊልሰን "የከፋው ቢመጣ እንኳ ቶሎ ነዋሪዎችን ሆስፒታል ለማድረስ ይጠቅሙናል በሚል ነው የተከራየናቸው"ይላል።

ቦልሶናሮ ምንድነው የሚሉት?

ቦልሶናሮ እንደ ትራምፕ ያሉ መሪ ናቸው። ከአፋቸው የሚወጣ ቃል ሁሌም የውዝግብ መነሻ ነው።

መጀመርያ አካባቢ ቫይረሱ ላይ ሲሳለቁ ነበር። በኋላ "ጋዜጠኞች የፈጠሩት የተጋነነ በሽታ ነው፤ ፍርሃት አትንዙብን" ሲሉ ቆዩ። የገዛ የጤና ሚኒስትራቸው የተናገሩትን ተቃረኑ። በቅርቡ ደግሞ ይባስ ብለው ደጋፊዎቻቸውን አሰልፈው ሲጨብጡ በቲቪ ታይተዋል።

"አታካብዱ፤ ሥራ እየሰራን በሽታውን መከላከል እንችላለን፤ ቤት መቀመጥ ብሎ ነገር የለም" ብለዋል ቦልሶናሮ።

ሰውየው ለሕዝባቸው የሚያስተላልፉት መልዕክት ሁሌም ችግር ያለበት ነው። በቅርቡ በቴሌቪዥን ብቅ ብለው ምንድነው እንዲህ መርበድበድ፤ ደግሞ ለጉንፋን… ብለዋል።

ከሰሞኑ ደግሞ ይባስ ብለው እንዲህ አሉ "ይቅርታ አርጉልኝና ምንም ማካበድ አያስፈልግም…ሰዎች ይሞታሉ ምንም ጥርጥር የለውም፤ ነገር ግን የትራፊክ አደጋ ይከሰታል ተብሎ የመኪና ፋብሪካ ይዘጋል እንዴ?"

ኮሮና
Banner