ኮሮናቫይረስ፡ በሶሪያ የመጀመሪያውን የኮሮናቫይረስ ሞት ተከትሎ ስጋት ነግሷል

ታትሟል

በእርስ በእርስ ጦርነት እየታመሰች በምትገኘዋ ሶሪያ አንዲት ሴት በኮሮናቫይረስ መሞቷን የአገሪቷ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ። ይህም በአገሪቷ በኮሮናቫይረስ የተመዘገበ የመጀመሪያው ሞት ሆኗል።

ሴትዮዋ ወደ ሆስፒታል ከተወሰደች በኋላ እሁድ ዕለት መሞቷን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። ቦታው ግን የት እንደሆነ አልገለጸም።

ሌሎች ተጨማሪ 9 ሰዎችም በቫይረሱ መያዛቸው የተገለጸ ሲሆን፣ በቫይረሱ የተጠረጠሩ ሰዎች ግን ቁጥራቸው ከፍ ያለ ነው።

በመሆኑም ቫይረሱ በጣም ተጋላጭ ወደሆኑት የህብረተሰብ ክፍሎች ይዛመታል የሚል ስጋት ፈጥሯል።

በሶሪያ 64 በመቶ የሚሆኑ የህዝብ የህክምና ተቋማት ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት የሚሰጡ ቢሆንም፣ የሰለጠነ ባለሙያ እጥረት ግን እንዳለ የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

በሶሪያ 6 ሚሊየን ሰዎች በአገር ውስጥ የተፈናቀሉ ሲሆን አብዛኞቹ የሚኖሩት በጣም በተጨናነቁ መጠለያዎች ነው።

እነዚህም የውሃ እጥረትና የንጽህና ችግር ያለባቸው ናቸው።

የአገሪቷን ትላልቅ ከተሞች የሚቆጣጠረው የፕሬዚደንት በሽር አላሳድ መንግሥት የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል።

ከእነዚህ መካከል በምሽት የሰዓት እላፊ፤ በግዛቶች መካከል የሚደረግ የጉዞ እገዳ፤ ትምህርት ቤቶች እና ዩኒቨርስተዎችን መዝጋት እንዲሁም መስጊዶችን ጨምሮ ሌሎች ስብሰባዎችን መከልከል ይጠቀሳሉ።

በተቃዋሚዎች ቁጥጥር ሥር ያለችው የሰሜን ምዕራቧ ግዛት ኢድሊብ፣ እስካሁን በኮቪድ -19 የተያዘ ሰው መኖሩ ያልተገለጸ ቢሆንም ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ግን በቦታው ያለው ሁኔታ አሳስቧቸዋል።

ከባለፈው ታህሳስ ጀምሮ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎች መንግሥት በሥፍራው የሚወስደውን አጸፋ በመሸሽ ቀያቸውን ጥለው ተፈናቅለዋል። በአካባቢው በጦርነት ለሚጎዱ ሰዎች የህክምና አገልገሎት የሚሰጡ ሆስፒታሎች ጥቂት ናቸው።

የአካባቢው የጤና ባለሥልጣናት የቫይረሱን ሥርጭት ለመግታት እየተዘጋጁ መሆኑን ቢገልጹም ድንበር የለሹ የሐኪሞች ቡድን ግን ተጨማሪ ድጋፍና የሚወሰዱ እርምጃዎች ከሌሉ የቫይረሱ ሥርጭት አደገኛ ሊሆን እንደሚችል አስጠንቅቋል።

ግብረሰናይ ድርጅቱ፤ 164 ሺህ ሰዎችን የሚያስተናግደውን ደሪ ሀሰን ካምፕን ጨምሮ በሁለት የጤና ተቋማት የምርመራ አገልግሎት እየሰጠ እንደነበር ገልጿል።

"ሁለት እና ሶስት ቤተሰቦች ከብርድና ከዝናብ እንኳን የማያስጥላቸውን አንድ ድንኳን ተጋርተው ሲኖሩ ተመልክተናል፤ አዳዲስ የሚመጡ ተፈናቃዮችንም ለማስተናገድ ያሉት ጥቂት ድንኳኖች ናቸው" ሲሉ የድርጅቱ ፕሮጀክት መሪ ያለውን ሁኔታ አስረድተዋል።