ኮሮናቫይረስ፡ ፊታችንን በእጃችን መንካት ለምን ልምድ ሆነብን? እንዴትስ መተው እንችላለን?

ታትሟል

በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በርካታ የጤና ባለሙያዎችና ባለስልጣናት ደጋግመው እንደሚመክሩት የኮሮናቫይረስ ወረርሸኝን ለመከላከል ቁልፍ ከሆኑ መንገዶች መካከል አንዱ ፊታችንን በእጃችን አለመንካት ነው።

ስናወራና የተለያዩ ነገሮችንን ስናከናውን ፊታችንን መነካካት የብዙዎቻችን ልምድ ነው። ነገር ግን በመጀመሪያ ደረጃ ለምንድን ነው ፊታችንን የምንነካው? አሁንስ ብድግ ብለን ለማቆም እንችላለን?

የሥነ ልቦና ባለሙያዋ ናታሻ ቲዋሪ እንደሚሉት ይህንን ልማዳችንን በቀላሉ ለመተው አስቸጋሪ ነው፤ ምክንያቱ ደግሞ "ከአፈጣጠራችን ጋር የተያያዘ በመሆኑ ነው።"

ባለሙያዋ እንደሚሉት በእጃችንን ፊታችንን መነካካት የተፈጥሯችን አካል ሆኗል። ለዚህም ምሳሌ ሲያስቀምጡ የሰው ልጅ በእናቱ ማህጸን ውስጥ እንኳን እያለ በደመ ነፍስ ፊቱን እንደሚነካካ ተናግረዋል።

ለእራሳችን ፊታችንን በእጃችን መንካት እንደሌለብን፣ መንካት ማቆም እንዳለብን ደጋግመን ብንነግርም፤ ፊታችንን ከነካን ልንታመም እንደምንችል ብናስብም፤ የምንላቸውና የምናስባቸው ነገሮች በሙሉ ከተፈጥሯችን ውጪ የሆነ ነገር ይሆናሉ።

ፊታችንን በምንነካካበት ጊዜ እያደረግን ያለነው እራሳችንን እያረጋጋን ወይም በአንድ ነገር ላይ ለማተኮር እየሞከርን ሊሆን ይችላል።

የሥነ ልቦና ባለሙያዋ እንደሚሉት በተለይ ከፊታችን የተለዩ ክፍሎችን በእጃችን ስንነካ በሰውነታችን ውጥረትን የሚያስተናግዱ የተወሰኑ ክፍሎችን እያነቃቃን ይሆናል። በዚህም ፓራሲምፓተቲክ የሚባለውን የነርቭ ሥርዓታችንን እናነቃቃለን። ይህም እራሳችንን ለማረጋጋት የሚያስችለን አንድ መንገድ ነው።

በውሾችና በድመቶች ላይም ተመሳሳይ ሁኔታ ማየት ይቻላል የሚሉት ባለሙያዋ፤ ህጻናትም ከወላጆቻቸው በመመልከት ተመሳሳይ ነገሮችን ያደርጋሉ ሲሉ ይገልጻሉ። እንደ ባለሙያዋ ከሆነ ቤተሰቦቻችን ሲደነግጡ፣ ሲበሳጩ ወይም ሲደነቁ ፊታቸውን በእጃቸው የሚይዙ ከሆነ፣ ልጆች ወላጆቻቸው የሚያደርጉትን የመድገም ሰፊ ዕድል አላቸው።

ግራ የሚያጋባው ግን ፊታችንን አለመንካት እጅግ ጠቃሚ በሚሆንበት ጊዜ ሳናስበው አእምሯችን በመደበኛነት እጃችንን ለጤናችን አስፈላጊ ወደሆነው ቦታ እንዲሄድ ያደርገዋል።

በእጃችን ፊታችንን እንዳንነካ ምን ማድረግ አለብን?

ፊታችንን ፈጽሞ በእጃችን አለመንካት የማይቻል ነገር በመሆኑ ይህንን ልማዳችንን ለማስወገድ ቁልፍ ዘዴ የሚሆነው ያዳበርነውን ልማድ መሰረት አድርገን ፊታችንን ደጋግመን እንድንነካ የሚያደርጉንን ነገሮች መቀነስ ያስፈልጋል።

በተጨማሪም እጃችንን ከፊታችን ጋር ያለውን መነካካት ለማስወገድ የሚያስችሉ ልማዶችን ማዳበርና እጃችንን የምናሳርፍበትን ቦታዎች መከታተልና መወሰን ጠቃሚ ነው።

ለምሳሌም ሲያወሩ እጅዎ ለፊትዎ በቀረበ ሁኔታ እያንቀሳቀሱ የሚናገሩ ከሆነ እጅዎ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ፊትዎ ላይ እንዲያርፍ እድልን ስለሚሰጠው ከፊትዎ ማራቅ ይኖርብዎታል።

ለዚህ ደግሞ ጣትዎትን በማቆላለፍ ጭንዎ ላይ እንዲያርፍ አድርገው እጅዎ ወደ ፊትዎ እንዳይቀርብ የሚያደርግ ልምድን ማዳበር ያስፈልጋል።

ከዚያም እጅዎን አንስተው ፊትዎን የመንካት ስሜት ሲፈጠርብዎ በርቀት ያለውን የእጅዎን እንቅስቃሴ በቀላሉ በመረዳት ምን ማድረግ እንዳለብዎ ለመወሰን ስለሚችሉ በደመ ነፍስ የሚያደርጉትን ነገር ለመቆጣጠር ይችላሉ።

ስለዚህም ፊታችንን የምንነካ ከሆነ ከሆነ እጃችን ንጹህ መሆን ይኖርበታል።

በተለይ የኮሮናቫይረስ በፍጥነት እየተዛመተ ባለበት በዚህ ዘመን ደግሞ ከፍጥረታችን ጀምሮ አብሮን የቆየውን እንዲሁም ለዓመታት ያዳበርነውን ፊታችንን የመንካት ልማድ ከተቻለ ማስወገድ ካልሆነም መቆጣጠር ያስፈልጋል።

ካልሆነ ደግሞ በተደጋጋሚ የእጃችንን ንጽህና በአግባቡ በመጠበቅ ከኮሮናቫይረስና ከሌሎች በሽታዎች እራሳችንን መጠበቅ እንዳለብን ባለሙያዎች ይመክራሉ።