ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ ሩዋንዳ ሙሉ ለሙሉ እንቅስቃሴዎችን አገደች
ሩዋንዳ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ሲባል ዜጎቿ ከቤት እንዳይወጡ አዛለች። ክልከላው በመላ አገሪቱ የሚጸና ነው ተብሏል።
ሩዋንዳ በአፍሪካ የመጀመሪያው የሆነውን ሙሉ ለሙሉ እንቅስቃሴን የማገድ እርምጃ ማስፈጸም ጀምራለች።
ይህ የአሀሪቱ እርምጃ በሁለት መልኩ አስተያየት እየተሰጣት ነው።
ትናንት በተጀመረው በዚህ እርምጃ መሰረት አገሪቱ በሁሉም አቅጣጫ የምትገናኝባቸው ድንበሮች ተዘጋግተዋል፤ ከቤት ውጭ መንቀሳቀስ የተከለከለ ሲሆን፤ ሱቆች፣ ገበያና መጠጥ ቤቶችም በራቸውን ዘግተዋል።
የመንግሥት ሰራተኞች ሥራቸውን ከቤታቸው ሆነው እንዲያከናውኑ መመሪያ ተላልፏል። ከውጭ አገራት የሚመጡ ሩዋንዳዊያንም ለ14 ቀናት መንግሥት ባዘጋጀው የለይቶ ማቆያ ቦታ የመቆየት ግዴታ ተጥሎባቸዋል።
ሩዋንዳ እስካሁን 19 የኮሮናቫይረስ ታማሚ ዜጎችን መለየት የቻለች ሲሆን ከምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛውን ቁጥር ይዛለች።
ሩዋንዳ የወሰደችውን እርምጃ ተከትሎ በማሕበራዊ ሚዲያ አንዳንዶቹ እርምጃው ቫይረሱን ለመከላከል ተገቢ መሆኑን በመደገፍ አሞካሽተዋል። በሌላ በኩል ገሚሶቹ ደግሞ እርምጃው በድንገት የተወሰደ በመሆኑ በሰዎች ሕይወት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል እያሉ ነው።
በዚህ በቤት ውስጥ የመቆየት እርምጃ በቀን ሥራ ተሰማርተው ኑሯቸውን የሚገፉ በሚሊዮን በሚቆጠሩ ሩዋንዳዊያን ላይ በተለየ ሁኔታ ችግር ሊደርስባቸው እንደሚችል ተገምቷል።
በቤት ውስጥ የመቀመጥ እርምጃው ለሁለት ሳምንታት የሚቆይ ሲሆን እንደ ሁኔታው ሊከለስ እንደሚችል ከሩዋንዳ ጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት የወጣው መረጃ ያመለክታል።