ኮሮናቫይረስ፡ የናይጄሪያ ሃኪሞች "ሰብዓዊነትን እናስቀድም" በሚል አድማቸውን አቆሙ

ታትሟል

ናይጄሪያ ውስጥ ሃኪሞች ለወራት ደመወዝ አልተከፈለንም በሚል ተቃውሞ ጠርተው ነበር። ነገር ግን አሁን በኮሮናቫይረስ ምክንያት አገሪቱ ከምንጊዜውም በላይ ሃኪም የሚያስፈልጋት ወቅት ላይ በመሆኗ "ለሰብዓዊነት ሲባል አድማውን እናቁም" ብለዋል።

የኮሮናቫይረስ ከደረሰባቸው የአፍሪካ አገራት አንዷ የሆነችው ናይጄሪያ እሁድ ዕለት አራት ተጨማሪ የኮሮናቫይረስ ታማሚዎችን ያገኘች ሲሆን በድምሩ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች 30 ደርሰዋል።

የናይጄሪያ የኮሮናቫይረስ መቆጣጠሪያ ማዕከል እንዳስታወቀው በአገሪቱ የተገኙ ሁሉም የቫይረሱ ተጠቂዎች [አራቱ ግለሰቦች] በሽታው በብዛት ከተከሰተባቸው አገራት ባለፈው ሳምንት የመጡ ናቸው።

ይህንንም ተከትሎ ከበሽተኞቹ ጋር ንክኪ አላቸው ያሏቸውን ሰዎች በመፈለግ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

እነዚህ አራት ተጨማሪ ተጠቂዎች መገኘታቸውን ተከትሎ ናይጄሪያ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት የሚወሰዱ እርምጃዎችን አጠንክራለች።

ይህንን ተከትሎም የባቡር ትራንስፖርትና ዓለም አቀፍ በረራዎች እንዲቆሙ ተደርጓል። በማንኛውም አውቶብስ ውስጥ በሚደረግ ጉዞም ወንበር ከሞላ መቆም እንደማይቻል መመሪያው ከልክሏል።

የመንግሥት ሰራተኞች ለሚቀጥሉት 14 ቀናት ቤታቸው ውስጥ እንዲቆዩ ተነግሯቸዋል። የግል ተቋማትም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስዱ የተነገራቸው ሲሆን አስፈላጊ የሆኑ ሰዎች ብቻ ቢሮ እንዲገቡ ምክረ ሃሳብ ተቀምጧል።

ባለስልጣናትም የባህል መሪዎች የሰዎችን መሰባሰብ እንዲያስቀሩና ሰዎች ቤታቸው ውስጥ ሆነው ይህን አስቸጋሪ ጊዜ እንዲያሳልፉ ጠይቀዋል።

ታዋቂው የናይጄሪያ ፖለቲከኛና የቢዝነስ ሰው አቲኩ አቡበከር የኮሮናቫይረስ እንዳለባቸው ካረጋገጡት አራት ሰዎች መካከል አንዱ የእርሳቸው ልጅ መሆኑን በትዊተር ገጻቸው ገልጸዋል። ልጃቸው ወደ ሆስፒታል ለህክምና እንደተወሰደ የገለጹት አቡበከር "በጸሎታችሁ አግዙኝ" ብለዋል።

አቲኩ አቡበከር በናይጄሪያ ፖለቲካ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ሲሆኑ በኦሉሴጉን ኦባሳንጆ የፕሬዝዳንትነት ዘመን (1999-2007 እ.አ.አ) 11ኛው የናይጄሪያ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው አገልግለዋል።