ኮሮናቫይረስ፡ በቅርቡ እስር ቤት የገባው ሃርቪ ዌንሰታይን በኮሮናቫይረስ መያዙ ተረጋገጠ

ሃርቪ ዌንሰታይን

የፎቶው ባለመብት, REUTERS

ታትሟል

ታዋቂው የሆሊዉድ ፊልም ፕሮዲዩሰር የነበረውና ወሲባዊ ጥቃት በመፈጸም እስር ቤት የገባው ሃርቪ ዌንስታይን በኮሮናቫይረስ መያዙ በምርመራ ተረጋገጠ።

የኒው ዮርክ ከተማ የማረሚያ ቤት መኮንኖችና ፖሊሶች ማኅበር ፕሬዝዳንት የሆኑት ማይክል ፓወርስ እንዳሉት ዌንስታይን በአሁኑ ጊዜ ከሌሎች ተለይቶ ክትትል እየተደረገለት ነው።

ዌንስታይን በአስገድዶ መድፈርና በወሲባዊ ጥቃት ተከሶ ባለፈው የካቲት ወር የ23 ዓመት እስር ተፈርዶበት ነው ወህኒ የወረደው።

ጠበቃው ግን በብይኑ ላይ ይግባኝ እንደሚጠይቅ አሳውቋል።

ዌንስታይን ኒውዮርክ ውስጥ በሚገኝበት እስር ቤት እሁድ ዕለት ሁለት እስረኞች በተደረገላቸው ምርመራ በኮሮና ቫይረስ ተይዘው መገኘታቸውን አንድ ፖሊስን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል።

የዌይንስታይን ጠበቃ እንዳለው ስለደንበኛው የኮሮናቫይረስ የምርመራ ውጤት የሕግ ቡድኑ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ አሳውቋል።

ጠበቃው ኢምራን አንሳሪ እንዳለው "የተባለው እውነት ከሆነ በጣም አሳሳቢ ነገር ነው። ዌንስታይን ያለበት የጤንነት ሁኔታን ከግንዛቤ በማስገባት ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተልን ነው።"

ዌይንስታይን በተለያዩ ጊዜያት በበርካታ ሴቶች ላይ ፈጽሞታል በተባለው ወሲባዊ ጥቃት ሳቢያ ከዓመታት በፊት ጀምሮ ክስ የቀረበበት ሲሆን የተወሰኑት ክሶች ውድቅ ተደርገውለታል፤ ይህ ባይሆን ኖሮ አሁን ከተፈረደበት የእስር ዘመን በላይ ቅጣት ይጠብቀው ነበር ተብሏል።

ከሦስት ዓመታት በፊት ቁጥራቸው የበዛ ሴቶች በሃርቪ ዌንስታይን ላይ አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ ያልተገባ ወሲባዊ ባህሪይን በማሳየት ክስ ከመሰረቱበት በኋላ ጉዳዩ ትኩረት አግኝቶ በቅርቡ ከ20 ዓመት በላይ እስር ተፈርዶበታል።

ኮሮና