የሱዳን የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር የእስር ትዕዛዝ ወጣባቸው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሱዳን አቃቤ ሕግ መስሪያ ቤት የቀድሞውን የአገሪቱ ከፍተኛ ሹም ወደ ማረሚያ ቤት እንዲጋዙ ትዕዛዝ አስተላልፏል። ይህ ትዕዛዝ የተላለፈባቸው ሹም የቀድሞው የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር የነበሩት አሊ ካርቲ ናቸው።
ከ30 ዓመት በፊት በፈረንጆቹ በ1989 ኦማር አልበሽር በመፈንቅለ መንግሥት ወደ ስልጣን ሲመጡ ሁነኛ የመፈንቅለ መንግሥቱ አቀናባሪ ነበሩ ተብለው ነው አሊ ካርት የእስር ትዕዛዝ የተላለፈባቸው።
አሊ ካርት ባለፉት ዓመታትም በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በብዛት ሲወቀሱ ቆይተዋል። በተለይ በ1990ዎቹ እርሳቸው የመንግስት ሹም ሆነው በደቡብ ሱዳን ለሚሊሻዎች ትዕዛዝ በመስጠት ከፍተኛ ጭፍጨፋ አስደርገዋል በማለት ይከሷቸዋል።
በዚህ ሳቢያም የሰብዓዊ መብት ጥሰቱ ተስፋፍቶ ደቡብ ሱዳን ውስጥ ከፍተኛ የሰብዓዊ ጥሰት መድረሱን የመብት ተሟጋቾቹ ይጠቅሳሉ።
በኦማር አልበሽር የስልጣን ዘመን አሊ ስለጉዳዩ ተጠይቀው 'የለሁበትም' የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። አሊ ከፈረንጆቹ 2010 እስከ 2015 ድረስ የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚንስትር በመሆን አገልግለዋል።
ባለፈው ዓመት በሕዝባዊ አመጽ ከስልጣን የተወገዱት ኦማር አልበሽር፤ በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በዘር ፍጅት ወንጀል ተጠርጥረው እየተፈለጉ ነው። ሱዳን ውስጥም ከስልጣን ሲወገዱ በነበረው ሕዝባዊ አመጽ ለደረሰው ግድያና ስልጣን ላይ በወጡበት ወቅት በተደረገው መፈንቅለ መንግሥት ለሞቱት ሰዎች ተጠያቂ ናቸው በሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
የአሁኑ የሱዳን መንግሥስት ለ30 ዓመታት ሱዳንን የመሩትን የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦማር አልበሽርን ለዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት አሳልፎ ለመስጠት ተስማምቷል።
ኦማር አልበሽር በሕዝባዊ አመጽ ከስልጣን ከወረዱ በኋላ፤ ከወታደሩ እና ከሲቪል በተውጣጣ ጥምር አስተዳደር የምትመራው ሱዳን ከወራት በፊት የቀድሞውን የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ዲፕሎማት አብደላ ሃምዶክን ጠቅላይ ሚንስትር አድርጋ ሾማለች።
ከሳምንታት በፊት ደግሞ በእኒሁ ጠቅላይ ሚንስትር ላይ የግድያ ሙከራ ተደርጎባቸው ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው መትረፍ ችለዋል።












