አሜሪካዊቷ እናት ከልጆቿ መጥፋት ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር ውላለች

የፎቶው ባለመብት, Police handout
ሁለት ልጆቿ ለወራት ጠፍተውባት የነበረችው እናት በአሜሪካዋ ግዛት ሃዋይ በቁጥጥር ስር መዋሏ ተዘግቧል።
ፖሊስ ላለፉት ወራት እጅግ የተወሳሰበ የፍለጋ ስራ ሲያከናውን እንደነበር ተገልጿል።
የ 46 ዓመቷ ሎሪ ደይቤል ባለፈው ሕዳር ወር ላይ ከልጆቿ ጋር በተገናኘ በፖሊስ ምርመራ ከተደረገባት በኋላ ወደ ሃዋይ ሄዳለች ተብሏል።
በሚያስገርም ሁኔታ የት እንደገቡ ካልታወቁት ህጻናት ጉዳይ ጋር በተያያዘ ሳይሆን አይቀርም የተባሉ ሶስት ሰዎች መሞታውን ፖሊስ አስታውቋል።
ሎሪ የዓለም መጨረሻ መቅረቡን የሚሰብክ አምልኮ ውስጥ ትሳተፍ እንደነበር የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። እስካሁን ሁለቱን ህጻናት ባለመንከባከብ ክስ ቀርቦባት በ 5 ሚሊየን ዶላር ማስያዣ ነበር የምትንቀሳቀሰው።
በቁጥጥር ስር ከዋለች በኋላ ባለፈው አርብ ፍርድ ቤት የቀረበች ሲሆን ለመጪው መጋቢት ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷታል።
ሎሪ የቀድሞ ባለቤቷ በወንድሟ ተተኩሶበት ከተደገለ በኋላ ከአሪዞና ወደ ኢዳሆ መኖሪያዋን ቀይራ ነበር። ወንድሟ ባለቤቷን የገደለው እራሱን ከአደጋ ለመከላል እንደሆነ የገለጸች ሲሆን ታህሳስ ወር ላይ እሱም ባልታወቀ ምክንያት ህይወቱ አልፋለች።
ህዳር ወር ላይ ፖሊስ ከልጆቹ አያቶች የስልክ ጥሪ ደርሶት ነበር። በጥሪውም ልጆቹንና ቤተሰቡን ሄደው እንዲጎበኙና ደህንነታቸውን እንዲያጣሩ ተነግሯቸው ነበር።
ፖሊስም ባደረገው ማጣራት ጆሹዋ ቫሎው የተባለው የ7 ዓመት ህጻንና ታይሊ ራይን የተባለችው የ 17 ዓመት ታዳጊ ከመስከረም ወር ጀምሮ በቤት ውስጥ እንዳልነበሩ ይደርስበታል።
ባለስልጣናት እንዳስታወቁት ሎሪ ፖሊሶች ጥያቄ ሲያቀርቡላት የተለያዩ አይነት ምላሾችን የሰጠች ሲሆን በአንዳንድ አጋጣሚዎች ደግሞ ዋሽታም ነበር። ፖሊሶች ልጆቹ የት እንደሚገኙ አጥብቀው ሲጠይቋት እንደውም እኔ ልጆች የሉኝም ብላለች።
በሚቀጥለው ቀን ደግሞ ከቤቷ የጠፋች ሲሆን ፖሊስም በቤቱ ውስጥ የነበረ አንድ ክፍልን በሚፈትሽበት ወቅት የልጆቹ ሳይሆኑ አይቀርም የተባሉ ልብሶችና የተለያዩ መጫወቻዎቸው ተገኝተዋል።
የቀድሞ ባለቤቷ ከመሞቱ በፊት ባስገባው የፍቺ መጠየቂያ ሰነድ ላይ እራሷን እንደ 'አምላክ' እንደምትመለክተትና በ 2020 እየሱስ ክርስቶስ በድጋሚ ሲመጣ ስራዎቹን እንደምታስፈጽምለት ታምን ነበር ብሏል።
አክሎም የእሷን መንገድ ለማደናቀፍ የሚሞክር ከሆነ እንደምትገለውና በድን አካሉንም ለማስወገድ መላእክት እንሚያግዟት እንደነገረችው አስፍሯል።
ሎሪ ከእነዚህ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ ጥፋተኛ ሆና ከተገኘች እስክ 14 ዓመት በሚደርስ እስር ልትቀጣ ትችላለች።
ከዚህ በፊት በሞርሞን ሀይማኖት ላይ መሰረት ያደረጉና የዓለም መጨረሻን የሚሰብኩ የተለያዩ መጽሀፍትን ያሳተመች ሲሆን ለዓለም መጨረሻ መዘጋጀት አለብን ብላ ታምን ነበር ተብሏል።












