ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከ47 ዓመታት በኋላ የተገናኙት የ98 እና የ101 ዓመት እህትማማቾች
በን ሰን እና በን ቺያ ካምቦዲያዊ እህትማማቾች ናቸው። 98 እና 101 ዓመት ሞልቷቸዋል።
እህትማማቾቹ ላለፉት 47 ዓመታት ተጠፋፍተው፤ አንዳቸው ስለሌላቸው በሕይወት መኖር አያውቁም ነበር።
በን ሰን እህቷ በካምቦዲያ በ1970ዎቹ በነበረው አገራዊ ነውጥ እንደሞተች ታስብ ነበር። በን ቺያም እህቷ በን ሰን በወቅቱ ሕይወቷ እንዳለፈ አምና ትኖር ነበር። እህትማማቾቹ ለመጨሻ ጊዜ የተያዩት እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ1973 ነበር።
የ98 ዓመቷ በን ሰን በሕይወት ያገኘችው እህቷን ብቻ አይደለም። የ92 ዓመቱ ታናሽ ወንድሟን በአይነ ሥጋ ለማየትም በቅታለች።
በወቅቱ በነበረው የካህመር ሮግ አገዛዝ ወደ 2 ሚሊዮን ሰዎች እንደሞቱ ይታመናል። በዛን ዘመን በርካታ ቤተሰቦች ተበትነዋል። የካህመር ሮግ አገዛዝ ልጆችን ከወላጆቻቸው በመለየት አገሪቱን አንቀጥቅጦ ይመራ ነበር።
የተባበሩት መንግሥታት የካህመር ሮግ አመራሮችን ለፍርድ በማቅረብ ሂደቱ ድጋፍ ያረደገ ሲሆን፤ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ 2009 ላይ የፍርድ ሂደቱ ተጀምሮ ሦስት የቀድሞ የካህመር ሮግ መሪዎች ብቻ ተፈርዶባቸዋል።
በን ሰን ባለቤቷን ያጣችው የቀድሞው የካምቦዲያ ጠቅላይ ሚንስትር ፖል ፖት ሥልጣን ላይ ሳሉ ነበር። አገዛዙ በ1979 ሲገረሰስ በካምቦዲያ መዲና በሚገኘው ቆሻሻ መጣያ ሰፈር አቅራቢያ መኖር ጀመረች።
ከተጣለ ቆሻሻ ውስጥ ዳግመኛ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል ቁሳቁስ እየሰበሰበች በመሸጥ ልጆቿን ታስተዳድር ነበር።
ካምፖንግ ቻም በተባለች ግዛት የምትገኘው የትውልድ መንደሯን ተመልሳ የመጎብኘት ፍላጎት ቢኖራትም፤ እድሜዋ ስለገፋና መራመድ ባለመቻሏ አልተሳካላትም።
ከ2004 ጀምሮ በን ሰንን እየደገፋት የነበረው 'ካምቦዲያን ችልድረንስ ፈንድ' የተባለው የተራድኦ ድርጅት፤ በን ሰንን ወደ ትውልድ ቀዬዋ ለመመለስ ሲወጥን እህትና ወንድሟ በሕይወት እንደሚገኙ ታወቀ።
እህትና ወንድሟ እዛው መንደር ውስጥ እየኖሩ ነበር።
በን ሰን ግማሽ ምዕተ ዓመት ገደማ ያላየቻቸውን እህትና ወንድሟን ያገኘችው በቅርቡ ነበር።
"የትውልድ መንደሬን ጥዬ ከወጣሁ ረዥም ጊዜ ሆኖኛል። እህቴና ወንድሜ እንደሞቱ ነበር የማስበው። ታላቅ እህቴን ዳግመኛ ማቀፍ መቻሌ አስደስቶኛል፤ ወንድሜ እንዳገኘኝ እጄን ሲይዘኝ ማልቀስ ጀመርኩ" ትላለች በን ሰን።
የበን ሰን እህት በን ቺያ ባለቤቷን ያጣችው በካህመር ሮግ አገዛዝ ዘመን ነበር። ባለቤቷ ሲሞት 12 ልጆች አፍርተው ነበር።
"13 ዘመዶቻችን በፖል ፖት ነው የተገደሉት። እህቴም የተገደለች መስሎኝ ነበር" ስትል በን ቺያ ትናገራለች።
አሁን እህትማማቹ ተለያይተው ያሳለፉትን ጊዜ ለማማካስ ብዙ ጊዜያቸውን አብረው ያሳልፋሉ። በቅርቡ ወደ ካምቦዲያ መዲና በጋራ ተጉዘው ነበር።
"ስለ እህቴ ሁሌም እናወራ ነበር። አያታለሁ ብዬ ግን አስቤ አላውቅም ነበር" በማለት በን ቺያ ደስታዋን ትገልጻለች።