ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የዘረፈው ካዝና ሕይወቱን የታደገው ሌባ
ማቲው ሀን ይባላል። አደንዛዥ እፅ መጠቀም የጀመረው ከታዳጊነቱ ጀምሮ ነበር።
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አልገፋበትም። በሱስ ሳቢያ ትምህርቱን አቋረጠ። አደንዛዥ እፅ የሚገዛበት ገንዘብ ሲያጥረው ኪስ አውላቂ ሆነ። ብዙም ሳይቆይ በድርጊቱ ዘብጥያ ወረደ።
በአውሮፓውያኑ 2001 ላይ ከአምስት ዓመት እስር በኋላ ተለቀቀ። ሆኖም ግን በድጋሚ ታሠረ። ፖሊስ ለሦስተኛ ጊዜ ሰርቆ ከተያዘ የእድሜ ልክ እስራት እንደሚጠብቀውም አሳወቀው።
ማቲው ከተለቀቀ በኋላ ሕይወቱን ለመለወጥ ይጣጣር ጀመር። መማር ጀመረ፣ ጥሩ ሥራም አገኘ። ነገር ግን የቅርብ ጓደኛው ራሱን ሲያጠፋ አደንዛዥ እፅ ወደመጠቀም፣ ወደስርቆትም ዳግመኛ ተመለሰ።
ካዝናው. . .
በ 2005 አንድ ምሽት ላይ ካዝና ሰረቀ። ይህ ካዝና የማቲውን ሕይወት እስከወዲያኛው የቀየረ ነበር።
"ካዝና ውስጥ ብዙ ነገር ነበር። ሽጉጥ፣ ፎቶግራፎች፣ የካዝናው ባለቤት ሰነዶች. . . ካገኘኋቸው ቁሶች ውስጥ የዲጂታል ካሜራ ካርድም ይገኝበታል። ካርዱን ኮምፒውተሬ ውስጥ ሳስገባው የካዝናው ባለቤት ህጻናት ላይ ወሲባዊ ጥቃት ሲያደርስ የሚያሳዩ ፎቶዎች ተመለከትኩ።"
ፎቶዎቹን ለፖሊስ ላስረክብ ቢል ካዝናውን መስረቁን መናዘዝ ሊኖርበት ሆነ። ይህ ደግሞ በገዛ እጁ 'እድሜ ልክ እሰሩኝ' እንደማለት ነው።
ማቲው መስረቁን ሳይናገር ወንጀለኛውን የካዝና ባለቤት የሚያጋልጥበትን መንገድ ያወጣ ያወርድ ጀመረ።
የዲጂታል ካሜራ ካርዱን ቦርሳ ውስጥ ከቶ፣ ከካዝናው ባለቤት ስምና አድራሻ ጋር አያይዞ፣ "ይህን አውሬ በቁጥጥር ሥር አውሉት" ከሚል መልዕክት ጋር ለፖሊሶች ላከ። እናቱ ስለጉዳዩ የሚወጣ ዜና እንዲከታተሉለትም ጠየቀ። ከሳምንት በኋላ ግለሰቡ መታሰሩን እናቱ በስልክ ነገሩት።
ፖሊሶች ጆን ሮበርትሰን አይቲከን የተባለውን የካዝና ባለቤት ሲያስሩት ማቲው ወደ ስርቆት ተመለሰ። ከስምንት ሳምንት በኋላ የሰረቀውን ቁስ በድረ ገፅ ሲሸጥ በፖሊስ ተያዘ።
ማቲውን በተደጋጋሚ ዘብጥያ ያወረዱት ፖሊሶች፤ ከተለቀቀ በኋላ ሕይወቱን ለማስተካክል እየሞከረ እንደነበር አስተውለው ነበርና 'ለምን ወደ ዝርፊያ ተመለስክ?' ሲሉ ጠየቁት። ምላሹ አጭር ነበር።
"ቢያንስ ቢያንስ ጆን ሮበርትሰን አይቲከንን አንድትይዙት ረድቻችኋለሁ"
ማቲው የፍርድ ሂደት ላይ ሳለ የጆንን ጉዳይ የያዙት አቃቤ ሕግ ምስክር ሁነን አሉት። በወቅቱ ማቲው ለሦስተኛ ጊዜ ሲዘርፍ ስለተያዘ የእድሜ ልክ እስራት ይጠብቀው ነበር።
ስለ ጆን ምስክርነት መስጠት ካዝናውን መዝረፉን በቀጥታ ማመን ማለት ነበር። "ምስክርነት ከሰጠሁ የራሴን ጉዳይ መከላከል አልችልም ማለት ነው" ሲል ሁኔታውን ያስታውሳል።
ምስክሩ እና እስረኛው ማቲው. . .
ጆን ቢያንስ የ25 ዓመት እስር ይጠብቀው ነበር። ይህን የሰሙ ሰዎች ማቲው ምስክርነት ከሰጠ የእድሜ ልክ እስራቱ እንዲቀነስለት ይጠይቁ ጀመር።
በስተመጨረሻ ማቲው 14 ዓመት ከአራት ወር ተፈረደበት። የታሰረው ግን ለሰባት ዓመታት ብቻ ነበር። ማቲው ከጆን ጋር በተመሳሳይ እስር ቤት የቆየበት ወቅትም ነበር። በጆን ጉዳይ ላይ ማቲው ምስክር ስለነበርም በተመሳሳይ ቀን ወደ ፍርድ ቤት ይወሰዱ ነበር።
"ወደ ፍርድ ቤት በመኪና ስንወሰድ እሱ በብረት በተዘጋ ክፍል ውስጥ ይገባል። እኔ ደግሞ በካቴና እታሰራለሁ። አብሬው በመኪና እየሄድኩ መሆኑን አያውቅም ነበር።"
ጆን እና ማቲው ተነጋግረው አያውቁም። ጆን አሁንም እስር ላይ ይገኛል። ማቲው ምስክርነት በመስጠቱም ደስተኛ መሆኑን ይገልጻል።
አዲስ መንገድ. . .
ማቲው እስር ቤት ሳለ የሕይወት መስመሩን መቀየር እንዳለበት ያስብ ነበር።
ከአደገኛ እፅ ለመላቀቅ ህክምና ጀመረ። ተመስጦ (ሜዲቴሽን) ያደርግ፣ ጆን ወሲባዊ ጥቃት ያደረሰባት ታዳጊ እናት የሰጡትን መጻሕፍትም ያነብ ነበር።
ከእስር ቤት ሲለቀቅ ዩኒቨረስቲ ገባ።
በኤሌክትሪክ ጠጋኝነት የሚሠራው ማቲው "ድንቅ ሥራ አለኝ፤ በቅርቡ ከባለቤቴ ጋር አዲስ ቤት ገዝተናል። ሕይወቴ በመልካም ነገሮች የተሞላም ነው" ሲል ይናገራል።
ማቲው የዛሬ አስር ዓመት ገደማ እስር ቤት ነበር። ዛሬ ግን የእኔ የሚለው መኖሪያ ባለቤት ነው።
የሰዎችን ቤት ይዘርፍ የነበረበትን ወቅት ሲያስታውስ ጸጸት ይሰማዋል።
"ለጥፋቴ ተቀጥቻለሁ። ከዚያ በኋላ የአደንዛዥ እፅ ሱሰኞች ከእኔ እንዲማሩ የሕይወት ታሪኬን አካፍላለሁ።"