በብሔራዊ መዝሙር ተሳልቀሻል የተባለችው ዘፋኝ ተከሰሰች

ታትሟል

የክሮሽያ ፕሬዘዳንት ቃለ መሀላ በፈጸሙበት ሥነ ሥርዓት ላይ ያቀነቀነችው ድምጻዊት የአገሪቱ ብሔራዊ መዝሙር ላይ ተሳልቀሻል ተብላ ተከሰሰች።

ጆሲፋ ሊሳክ የተባለችው ድምጻዊት የአገሪቱን ብሔራዊ መዝሙር ያቀረበችው፤ በመዝሙሩ ላይ ለውጥ ካደረገች በኋላ ነበር።

ቦስኮ ዙፓኖቪክ የተባሉ የክሮሽያ ጠበቃ፤ ጆሲፋ ሆነ ብላ የአገሪቱ ብሔራዊ መዝሙር ላይ ተሳልቃለች ቢሉም፤ የድምጻዊቷ አሳታሚና የሙዚቀኞች ማኅበር ክሱ የዘፋኟን የፈጠራ መብት የተጋፋ ነው።

በክሮሽያ ሕግ መሰረት ብሔራዊ መዝሙርን አለማክበር የአንድ ዓመት እስርን ያስከትላል።

ጆሲፋ 'አወር ቢውቲፉል ሆምላንድ' ማለትም ውቧ አገራችን የተሰኘውን የክሮሽያ ብሔራዊ መዝሙር ባለፈው ማክሰኞ መድረክ ላይ ያቀረበችው በጃዝ ፒያኒስት ታጅባ ነበር።

ብሔራዊ መዝሙሩን ያቀረበችበት መንገድ፤ መዝሙሩ ሲዘጋጅ ያስተላልፍ ከነበረው ጸለምተኛ ስሜት የተለየ ነው የተባለ ሲሆን፤ ጠበቃው በበኩላቸው መዝሙሩ ድምጻዊቷ በፈለገችው መንገደ ተቀይሮ መቅረቡ በማኅበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት የለውም ብለዋል።

"የቀረበበት መንገድ አገሪቱ ላይ ለመሳለቅ ያለመ ነው፤ ቅሬታ ያቀረብኩትም ብሔራዊ ግዴታዬ ስለሆነ ነው" ሲሉም ተናግረዋል።

የድምጻዊቷ አሳታሚና የሙዚቀኞች ማኅበር በጋራ ባወጡት መግለጫ፤ "ሰብዓዊ መብትና የባህል እሴት የማይከበርበት ማኅበረሰብ ውስጥ እንደምንኖር ያሳያል" ብለዋል። ድምጻዊቷ ስለቀረበባት ክስ በአደባባይ አስተያየት እንደማትሰጥም አክለዋል።

ላለፉት 53 ዓመታት ስመ ገናና የሆነችው የ70 ዓመቷ ጆሲፋ በርካታ ሽልማት አግኝታለች።