በኃይል የታጠቁ ወታደሮች በድንገት በኤል ሳልቫዶር ፓርላማ ተገኝተው ጥያቄ አቀረቡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በከፍተኛ ሁኔታ የታጠቁ በርካታ ፖሊሶችና ወታደሮች ባልተጠበቀ መልኩ ኤል ሳልቫዶር ፓርላማ ገብተው የ'አስታጥቁን' ጥያቄያቸውን አቀረቡ።
ታጣቂዎቹ በፓርላማው የተገኙት የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ለጉባኤው ንግግር ለማድረግ ሳሉ ነበር።
ወታደሮቹ እና ፖሊሶቹ ጥያቄ፤ የተሻለ ትጥቅ እንዲኖራቸው የሚያስችለውን 109 ሚሊዮን ዶላር ብድር ፓርላማው ያፅድቅ የሚል ነበር።
ከቀናት በፊት ፕሬዝዳንት ናይብ ቡኬሌ የዚህን ብድር ሰነድ ተመልክተው እንዲያፀድቁ ለህዝብ እንደራሴዎቹ የሰባት ቀናት ገደብ ሰጥተው ነበር።
ተቃዋሚ ፖለቲከኞች የወታደሮቹን ድንገት በፓርላማ መገኘት ማስፈራሪያ ነው ሲሉ ተችተዋል።
ኤል ሳልቫዶር አለም ላይ ከፍተኛ ወንጀል የሚፈፀምባት አገር ስትሆን ብዙ ግድያዎችና ሌሎች ወንጀሎች የሚፈፀሙት ደግሞ በተደራጁ ወንጀለኛ ቡድኖች ነው።
እንደ አውሮፓውያኑ በ2019 ወደ ስልጣን የመጡት ፕሬዝዳንት ቡኬሌ በማዕከላዊ አሜሪካ የምትገኘው 'ኤል ሳልቫዶር የተደራጁ ወንጀለኞች መፈንጫ መሆንን ታሪክ አደርጋለሁ፤ ሙስናንም እዋጋለሁ' ብለው ቃል ገብተው ነበር።
ስለዚህም ነው የ38 ዓመቱ የኤል ሳልቫዶር ፕሬዝዳንት ፖሊስና ወታደሮችን በደንብ ማስታጠቅ የሚያስችላቸው ብድር እንዲፀድቅ የሚፈልጉት።
በጀቱ ከፀደቀ የፖሊስ መኪናዎችን፣ ሄሊኮፕተሮች፣ የቅኝትና የቁጥጥር መሳሪያዎች እንዲሁም የፀጥታ ሃይል የደንብ ልብስ ለመግዛት ይውላል ተብሏል።
ምንም እንኳ ፕሬዝዳንቱ ለህዝብ እንደራሴዎቹ በጀቱን እንዲያፀድቁ ቀነ ገደብ ቢያስቀምጡም ቅዳሜና እሁድ የፓርላማ አባላቱ ፓርላማ ሳይገኙ ቀርተዋል። ጉባኤው አለመሟላቱን የተመለከቱት ቡኬሌም ወደ ፓርላማው ኑ ሲሉ ለደጋፊዎቻቸው ጥሪ አስተላልፈዋል። በጥሪው መሰረት 50 ሺህ የሚሆኑ የመንግሥት ደጋፊዎች አደባባይ ወጥተዋል።
ፕሬዘዳንቱም የህዝብ እንደራሴዎቹ በጀቱን በተቀመጠው ቀን የማያፀድቁት ከሆነ ለድጋፍ ትወጣላችሁ ሲሉ እንዲመለሱ ጥሪ አስተላልፈው ነበር።
ከዚህ በመነሳት ተቀናቃኞቻቸው ፕሬዝዳንቱን ሊያስፈራሩን እየሞከሩ፤ አምባገነንም እየሆኑ ነው ሲሉ ይተቿቸዋል።














