ኬንያውያን የቀድሞ ፕሬዝዳንታቸው አራፕ ሞይን በእንባ ተሰናበቱ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኬንያውያን በታሪካቸው ለረጅም ዓመታት ሀገራቸውን የመሩትን የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዳንኤል አራፕ ሞይን ተሰናብተዋል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት አስከሬን በሬሳ ሳጥን ውስጥ ሆኖ ለመመልከትና የመጨረሻ ስንብት ለማድረግ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችም በመዲናዋ ናይሮቢ ተሰልፈው ታይተዋል።
ፕሬዝዳንት ሞይ በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር ከ 1978 እስከ 2002 ድረስ ኬንያን የመሩ ሲሆን፤ ባሳለፍነው ሳምንት ማክሰኞ ዕለት ነበር ህይወታቸው ያለፈው።
የሞይ አስከሬን ወደ ትውልድ መንደራቸው ከመወሰዱ በፊት ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ''ታላቅ መሪ'' ነበሩ ብለዋል።
ምንም እንኳን ሞይ በፕሬዝዳንትነት ዘመናቸው ሀገሪቱን በማረጋጋትና ኢኮኖሚው ጠንካራ እንዲሆን በማድረጋቸው ከደጋፊዎቻቸው ውዳሴ ቢያገኙም በርካታ ተቺዎች ግን አምባገነን መሪ ነበሩ ይሏቸዋል።
ማስጠንቀቂያ : አንዳንድ አንባቢያን ከታች ያለው ምስል ሊያስደነግጣቸው ይችላል
ፕሬዝዳንት አራፕ ሞይ የምሥራቅ አፍሪካዋን አገር ኬንያን በበላይነት ለ24 ዓመታት የመሩ ሲሆን፤ አገሪቱ ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነፃነቷን ከተቀዳጀች በኋላ ስልጣን የያዙ ሁለተኛው ፕሬዝዳንት ነበሩ።
በሥልጣን ላይ በነበሩበትም ወቅት ሃገሪቷን በጠንካራ ክንዳቸው ገዝተዋል የሚባሉት ዳንኤል አራፕሞይ፤ በሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሚተቿቸው አሉ።

የፎቶው ባለመብት, EPA
ሟች ፕሬዝዳንታቸውን ለመሰናበት በርካቶች ተሰልፈው የታዩ ሲሆን አንዳንዶቹን ቢቢሲ አነጋግሯቸው ነበር።
የ 46 ዓመቷ አን ንጃምቢ የቀድሞ ፕሬዝዳንቱን አስከሬን ለመመልከትና የመጨረሻ ስንብት ለማድረግ 100 ኪሎ ሜትሮችን እንደተጓዘች በመግለጽ '' ለታላቁ መሪ ያለኝን ክብር ለመግለጽ ነው የመጣሁት'' ብላለች።
'' ትምህርት ቤት እያለን በነጻ የሚሰጠንን ወተት አልረሳውም፤ እሳቸውንም ቢሆን አልረሳቸውም፤ እጅግ ለጋስ ሰው ነበሩ''
ሌላኛዋ ቀድሞውን ፕሬዝዳንት ለመሰናበት 600 ኪሎ ሜትሮችን የተጓዘችው ሄለን ንጌማ በበኩሏ ''ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን እንድከታተል ፕሬዝዳንቱ የገንዘብ ድጋፍ አድርገውልኝ ነበር ብላለች።
ፕሬዝዳንት ሞይ በነገው ዕለት (ማክሰኞ) ከናይሮቢ 200 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በሚገኘው የግል መኖሪያ ቤታቸው የቀብር ስነስርአታቸው የሚፈጸም ሲሆን ብሄራዊ የሀዘን ቀን እንደሚሆንም ይጠበቃል።
የመጀመሪያው የኬንያ ፕሬዝዳንት ጀሞ ኬንያታ መሞታቸውን ተከትሎ ወደ ስልጣን የመጡት አራፕ ሞይ በመጀመሪያዎቹ የስልጣን ዘመናቸውም 'ፈለግ' የሚለውን ቃል በሚተካው ስዋሂሊ "ንያዮ" መፈክር በርካታ ተከታዮችን አፍርተዋል።
አገሪቱንም አሁን ወዳለችበት የዕድገት ደረጃ እንድትገባ መንገድ ማስጀመር እንደቻሉ ይነገራል።
ነገር ግን በጎርጎሳውያኑ 1982 የተደረገባቸው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በአንድ ጊዜ ወደ አምባገነንነት ቀይሯቸዋል። በዚህም ሳቢያ በርካቶች ወደ እስር ቤት እንዲወረወሩ ሆነዋል።
ሞይ ኬንያን ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በብቸኝነት ሲመሩ ቆይተው በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ግፊት ነበር እንደ ጎርጎሳውያኑ 1992 ሌሎች ፓርቲዎች ወደ ምርጫው መድረክ እንዲመጡ የፈቀዱት።












