ቡርኪና ፋሶ ጽንፈኛ ኃይሎችን ለመዋጋት በሚል ዜጎቿን ልታስታጥቅ ነው

በቡርኪናፋሶ የሚገኝ ወታደር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የቡርኪና ፋሶ መንግሥት በቀጠናው እያደገ የመጣውን የጽንፈኛ ኃይሎች ጥቃትን ለመግታት ዜጎቹን ሊያስታጥቅ መሆኑን አስታውቋል።

የቡርኪና ፋሶ መንግሥት ጸንፈኞች የሚያደርሱትን ጉዳት ለመቀነስ የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ይገኛል። ከእነዚህም መካከል ፍቃደኛ የሆኑ ዜጎችን ማሰታጠቅ አንዱ ነው።

ባለፉት 30 ቀናት ብቻ በጽንፈኛ ኃይሎች በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል ደረሱ በተባሉ ጥቃቶች ቢያንስ 50 ሰዎች ተገድለዋል።

የአገሪቱ የህዝብ እንደራሴዎች በሚስጥር በተሰጡት ድምጽ ጽንፈኞችን ለመዋጋት የአገሪቱን ዜጎችን ለማስታጠቀው ወስነዋል።

ለአል-ቃይዳ እና አይኤስ አጋርነታቸውን የሰጡ ቡድኖች የሚያደርሱትን ጥቃቶች ሽሽት ቀያቸውን ጥለው የተሰደዱ የቡርኪና ፋሶ ዜጎች ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሆኗል።

የአገሪቱ ጸጥታ አስከባሪ መዋቅር ታጥቆ የሚንቀሳቀስ ጽንፈኛ ቡድን የመግታት ብቃት እና የአሃዝ ብልጫ የለውም ይባላል።

"በዚህም የአገሪቱ ዜጎች እራሳቸውን እና አገራቸውን ለመከላከል ጽኑ ፍላጎት እና ዝግጅት አሳይተዋል" ተብሏል።

ይህ የመንግሥት ውሳኔ ግን በጎሳ፣ በውሃ እና በግጦሽ መሬት ይገባኛል ምክንያት ግጭት ውስጥ የሚገባን ማህብረሰብ ማስታጠቅ መዘዙ ብዙ ነው የሚሉ አልጠፉም።

ማንኛውም እድሜው ከ18 ዓመት በላይ የሆነ የቡርኪና ፋሶ ዜጋ ሊታጠቅ ይችላል።

መስፈርቱም በጎ ፍቃደኞች አገራዊ ፍቅር ያላቸው እና በማንኛውም ጊዜ መስዕዋትነት ለመክፍል ዝግጁ መሆን ይኖርባቸዋል ተብሏል።

ከእያንዳንዱ መንደር ወይም የመኖሪያ አከባቢዎች ቢያንስ 10 ሰዎች የሚመለመሉ ሲሆን፤ ከዚያም የ14 ቀናት መሠረታዊ የውትድርና ስልጠና ይወስዳሉ።

በስልጠናውም የጦር መሳሪያ አጠቃቀም፣ መሠረታዊ የውጊያ ስልቶች፣ ወታደራዊ ስነ-ምግባር እና የግብረገብነት ትምህርቶች ተካትተዋል።

ተመልምለው የሚታጠቁ ዜጎች ለሚቀበሏቸው ግዴታዎች ከመንግሥት የገንዘብ ድጋፍ ሊያገኙ እንደሚችሉ እና በግዴታ ወቅት ጉዳት ቢያጋጥማቸው ካሳ ይከፈላቸዋል ተብሏል።