ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
በታንዛንያ አምልኮ ቦታ በተከሰተ መረጋገጥ 20 ሰዎች ሞቱ
በታንዛንያ በአምልኮ ቦታ በተከሰተ መረጋገጥ ሃያ ሰዎች መሞታቸው ተዘግቧል።
በሰሜናዊ ታንዛንያ 'ሞሺ' ከተማ በሚገኝ ስታዲየም የፕሮቴስታንት አማኞች አገልግሎት ላይ በነበሩበት ወቅት ቅዳሜ እለት አደጋው መከሰቱ ተነግሯል።
የሞሺ ግዛት ኮሚሽነር ኪፒ ዋሪዮባ እንዳሉት መረጋገጡ የተፈጠረው ቅብዓ ቅዱስ (የተቀደሰ ዘይት) ለመቀበል በተደረገ ግፊያ ነው።
የታንዛንያ ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፉሊ የኃዘን መግለጫቸውን ባስተላለፉበት ወቅት በእንደዚህ ትልልቅ ቦታዎች ላይ የሚደረጉ ዝግጅቶች ላይ የተሻለ የቁጥጥር ስርአት ያስፈልጋል ብለዋል።
አገልግሎቱን ሲመሩ የነበሩት ራሳቸውን 'ሐዋርያ' ብለው በሚጠሩት ፓስተር ቦኒፋስ ምዋፖሳ ናቸው።
በቦታው የነበሩ ሰዎች እንደገለፁት ፓስተሩ በቦታው ለተሰበሰበው ህዝብ ቅብዓ ቅዱስ (የተቀደሰ ዘይት) መሬት ላይ እንደፈሰሰና በዛም እንዲተላለፉ መጠየቃቸውን ነው።
ህዝቡ ከህመሜ እድናለሁ በሚል ተስፋ ዘይት የተደፋበትን ቦታ ለመርገጥ መሯሯጥ ጀመሩ።
በአገልግሎቱ ታዳሚ የነበረው ፒተር ኪሌዎ ሁኔታውን "አስደንጋጭ" በማለት የገለፀው ሲሆን "ሰዎች ያለምንም አይነት ምህረት ሲጠላለፉ እንዲሁም በክርናቸው ሲጎሻሸሙ" ነበር በማለት ለአጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ተናግሯል።
አክሎም "ሰባኪው ዶላር የበተነ ይመስል ነበር" ብሏል።
አደጋውን ተክትሎም ፓስተሩ ለጥያቄ ይፈለጋሉ ተብለው በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል።
ኮሚሽነሩ አክለው እንደገለፁት ተጨማሪ ሞቶች ተከስተው እንደሆነ ለማረጋገጥ ወደ አካባቢው የጤና ተቋማት ሰዎች አሰማርተዋል።
"አደጋው የተከሰተው ምሽት ላይ ነው። በቦታውም ብዙ ህዝብ የነበረ እንደመሆኑ መጠን ሌሎች ሟቾች እንደሚኖሩ እናስባለን። ሁኔታውንም እየገመገምን ነው" ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።