የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነትን የሚቃወሙት ታንዛንያዊ ባለስልጣን አሜሪካ እንዳይገቡ ተከለከሉ

ታትሟል

የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያንን የሚያድን የክትትል ቡድን አቋቁመው ወከባ ያደርሳሉ የተባሉት የታንዛንያ ሚኒስትር አሜሪካ እንዳይገቡ ተከልክለዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ የመዲናዋ የዳሬሰላም የስራ ኃላፊ የሆኑት ፓውል ማኮንዳ "ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊ መብት ጥሰት ላይ ተሳትፈዋል" በማለት ወንጅሏቸዋል።

ከሳቸው በተጨማሪ የቅርብ ቤተሰቦቻቸውም አሜሪካ እንዳይገቡ ተከልክለዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፔ በትዊተር ገፃቸው ላይ እንዳሰፈሩት የማኮንዳ እገዳ የመጣው በታንዛንያ የሚደርሰው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አስጊ ደረጃ ላይ በመድረሱ ነው ብለዋል።

"ፓውል ማኮንዳ ተቃዋሚ ፖለቲከኞች ላይ ጫና በማሳረፍ፣ በመናገር ነፃነት ላይ የሚሰሩ ማህበራትን በመጨቆንና አንዳንድ ቡድኖች ላይ ጥቃት በማድረሳቸው" ይህ እገዳ ሊተላላለፍባቸው እንደቻለም የውጭ ጉዳይ ቢሮ በመግለጫው አትቷል።

በቀጥታ ፓውል ማኮንዳን በስም ጠርቶ በወነጀለው መግለጫ የዜጎችን የመኖር መብት፣ ደህንነትን በመጣስ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን ፈፅመዋል ብሏቸዋል።

የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት አፍቃሪያንን አድኖ የሚይዝ የክትትል ኃይል ከሁለት አመታት በፊት ያቋቋሙት ፓውል ዓለም አቀፉ ትችት የሚጠብቁት እንደሆነ ገልፀው "አምላኬን ከማስቆጣ እነዚህ አገራትን ባስቆጣ ይሻላል" ብለዋል።

የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት በታንዛንያ ወንጀል ነው።

በጎርጎሳውያኑ 2015 ስልጣን ላይ የመጡት ፕሬዚዳንት ጆን ማጉፊሊን ተከትሎ የመናገር ነፃነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሽቆለቆለ እንደሆነ ተገልጿል።

ፕሬዚዳንቱ በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ዘንድ የመብት አቀንቃኞችን በማሰር እንዲሁም ሚዲያን በማፈን በከፍተኛ ሁኔታ ይተቻሉ።