ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአፍሪካ ዋንጫ በየአራት ዓመቱ እንዲካሄድ ሀሳብ ቀረበ
የፊፋ ፕሬዝዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖ የአፍሪካ ዋንጫ በየሁለቱ ዓመቱ መካሄዱ ቀርቶ በአራት አመት አንዴ ብቻ አንዲካሄድ ለአፍሪካ እግር ኳስ ማህበር (ካፍ)ሃሳባቸውን አቅርበዋል።
ኢንፋንቲኖ በሞሮኮ እየተካሄደ በሚገኘው የካፍ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር '' በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደው አፍሪካ ዋንጫ አውሮፓውያኑ ከሚያስገኙት ሲነጻጸር ገቢው በሃያ እጥፍ ያነሰ ነው። በዚህ አካሄድ በየሁለት ዓመቱ ማካሄዱ አዋጪ ነው? እስቲ በየአራት ዓመቱ ማካሄድን ከግምት ውስጥ እናስገባው'' ብለዋል።
ቀጣዩ የአፍሪካ ዋንጫ በጎርጎሳውያኑ 2021 በካሜሩን አዘጋጅነት የሚካሄድ ሲሆን ልክ እንደ ቀድሞው ጥርና የካቲት ላይ ሀገራት ውድድር ያደርጋሉ።
ባለፈው ዓመት የአፍሪካ ዋንጫ ቀድሞ ከሚካሄድበት ወቅት በተለየ መልኩ ሰኔ እና ሐምሌ ላይ ግብጽ ውስጥ ተካሂዶ ነበር። በዚሁ ውድድር ተሳታፊ ሀገራት ቁጥርም ወደ 24 ከፍ እንዲል ተደርጓል።
የፊፋው ፕሬዝዳንት በንግግራቸው አክለውም ''ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄዎችን ማዘጋጀት ያስፈልጋል። በእኛ በኩል ሶስት መፍትሄ የሚያስፈልጋቸው ነጥቦችን ለይተናል፤ እነሱም ዳኝነት፣ መሰረተ ልማት እና ውድድሮች ናቸው'' ብለዋል።
አክለውም'' አሁን ስለአፍሪካ እግር ኳስ እድገት ብቻ የምናወራበት ሰአት ሳይሆን እርምጃ የምንወስድበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው። የትኛውም የአፍሪካ ሀገር ዓለም ዋንጫን አሸንፎ አያውቅም፤ ለምን ብለን መጠየቅም ይገባናል።''
ከዳኝነት ጋር በተያያዘ ፊፋ የተመረጡ 20 ዳኞችን በገንዘብና በስልጠና በመገደፍ ለአህጉሪቱ እግር ኳስ እድገት የበኩላቸውን እንዲወጡ ለማድረግ እንዳሰበም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የአፍሪካ እግር ኳስ አሁን ካለበት ደረጃ ከፍ በማድረግ በዓለማቀፍ ደረጃ ተፎካካሪ ለማድረግ ፊፋ 1 ቢሊየን ዶላር ፈሰስ ለማድረግና በእያንዳንዱ አባል ሀገር አንድ ዘመናዊ ስታዲየም ለመገንባት እቅድ መያዙም በስብሰባው ላይ ተገልጿል።