በየመኑ ጥቃት የሟቾች ቁጠር 111 ደረሰ

የፎቶው ባለመብት, AFP
በየመን አንድ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ላይ ቅዳሜ ዕለት በተፈጸመው የሚሳኤል ጥቃት የሟቾች ቁጥር በትንሹ 111 መድረሱን የሀገሪቱ ባለስልጣናት አስታወቁ።
ሚሳኤሉ የተተኮሰው በወታደራዊ ማሰልጠኛው ውስጥ በሚገኝ መስጂድ ውስጥ ወታደሮች የምሽት ጸሎታቸውን በማድረስ ላይ እያሉ ነበር ተብሏል።
መንግስት ጥቃቱን የፈጸሙት የሁቲ አማጺያን ናቸው ቢልም ቡድኑ ግን ለጥቃቱ ወዲያው ሀላፊነት ከመውሰድ ተቆጥቧል። በየመን የዛሬ አምስት ዓመት የእርስ በርስ ጦርነቱ ከተጀመረ ወዲህ ይሄኛው ጥቃት እጅግ ዘግናኝ ከሚባሉት መካከል እንደሆነም ተገልጿል።
በሳኡዲ የሚደገፈው መንግስት ታማኝ ወታደሮች እና የሁቲ አማጺያን መካከል የሚደረገው ጦርነት ሀገሪቱን ከማፈራረስ አልፎ እስካሁን ለ 100 ሺ የሚደርሱ ሰዎች ህይወት መጥፋት ምክንያት ሆኗል።
በየመን ከ 11 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ዜጎች የዕለት ጉርሳቸውን ለማግኘት የሚቸገሩ ሲሆን 240 ሺ የሚሆኑት ደግሞ ለከባድ ረሀብ የቀረበ በሚባል ደረጃ ህይወታቸውን ይመራሉ ብሏል የዓለም የምግብ ፕሮግራም።
በአማጺያን ቁጥጥር ስር ከምትገኘው ሳናአ በምስራቅ በኩል 170 ኪሎሜትሮች ርቀት ላይ የሚገኘው አል ኤስቲቅባል የተባለው ወታደራዊ ካምፕ ላይ በደረሰው ይህ ጥቃት 80 ወታደሮች ወዲያውኑ መሞታቸው ታውቋል።
ነገር ግን በሚሳኤል የተደረገው ጥቃት ከፍተኛ ስለነበረ ጉዳት አጋጥሟቸው የነበሩ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል። በዚህም የሟቾች ቁጥር ቢያንስ 111 እንደደረሰ ተገልጿል።
'ኤኤፍፒ' የተባለው የዜና ወኪል ደግሞ ከወታደሮችና የህክምና ባለሙያዎች አገኘሁት ባለው መረጃ መሰረት የሟቾች ቁጥር ከ 116 በላይ ይደርሳል።
የየመኑ ፕሬዝዳንት አብደራቡህ ማንሱር ሃዲ ከጥቃቱ በኋላ '' የከሀዲዎችና የሽብረተኞች ተግባር ነው'' ብለዋል ጥቃቱን። አክለውም ''የሁቲ አማጺያን ለሰላም ምንም አይነት ፍላጎት እንደሌላቸው ማሳያ ነው'' ብለዋል።
የሳኡዲ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በበኩሉ ጥቃቱን ''አማጺዎቹ ሁቲዎች ክብር ላለው የእምነት ቦታ እና ለየመን ዜጎች ህይወት ምንም ክብር እንደማይሰጡ ማሳያ ነው'' ብሎ ገልጾታል።












