ቦንብ የሚዘንብባትን የሶሪያ ከተማ አልለቅም ያለው የነፍስ አድን ሰራተኛ

በቦንብ የምትጋየውን ከተማ አልለቅም ያለው የነፍስ አድን ሠራተኛ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በቦንብ የምትጋየውን ከተማ አልለቅም ያለው የነፍስ አድን ሠራተኛ
ታትሟል

ቦንብ የሚዘንብባትን ሶሪያዊት ከተማ አልለቅም ያለ አንድ የነፍስ አድን ሰራተኛ ከቤተሰቡ ተነጥሎ ኑሮውን ቀጥሏል።

ለመጨረሻ ጊዜ በተቃዋሚዎች በተያዘችው የሶሪያ ግዛትና ግማሽ ክፍሏ በቦምብ በወደመው ሳራቄብ ከተማ ውስጥ አሁንም ጥቂቶች ነገን ተስፋ አድርገው ይኖራሉ። እስከቅርብ ጊዜ ድረስ ከ60,000 በላይ ሰዎች መኖሪያ ቤታቸው አድርገው ከተማዋን ይኖሩባት ነበር፣ ነገር ግን ባለፉት ጥቂት ወራት ውስጥ አብዛኛዎቹ ቤተሰቦች ከሚፈጠረው የቦንብ ፍንዳታ፣ ረሀብ እና ከበጋው ቅዝቃዜ ለማምለጥ ሲባል ከተማዋን ጥለው ሸሽተዋል።

ከፍርስራሿ ከተማ ጋር ሕይወታቸው እንዲጣበቅ ከተደረገው ጠንካራ ቡድን መካከል የሲቪል ፈቃደኛ የነፍስ አድን ሠራተኛ የሆነው ሌይት አል አብዱላሂ አንዱ ነው።

የ42 ዓመቱ ሌይት በአገሩ ሶሪያ ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት በአካባቢው የገንዘብ ልውውጥ ኩባንያ ውስጥ አካውንታት ነበር። ዳጎስ ያለ ገንዘብም ይቆጥር ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን ሌይት የሚቆጥረው በቦምብ በተፈረካከሰ የፍርስራሽ ክምር ውስጥ ቆፍሮ የሚያወጣቸውን በሞትና በሕይወት መካከል የሚገኙ ሰዎችን ነው።

በዚህ አደጋ ምክንያት በርካቶች ቤታቸውን ተሰናብተው ተሰደዋል በመካከል ከተተወ ቤታቸው ለመመለስ በመንገድ ላይ እያሉ ብዙዎቹ በሶሪያ ወይም በሩሲያ የቦምብ ጥቃቶች በተከናወኑ የአየር ጥቃቶች ተደብድበዋል።

በቦምብ የፈራረሰችው የሳራቄብ ከተማ

የፎቶው ባለመብት, Empics

የምስሉ መግለጫ, በቦምብ የፈራረሰችው የሳራቄብ ከተማ

አካባቢውን ለቅቀው ከሄዱት የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል የሌይት ሁለት ልጆቹና ባለቤቱ ይገኙበታል። እርሱ ግን እርዳታ ቢደረግላቸው ሊተርፉ የሚችሉ በርካታ ዜጎች ከሞት ጋር ተፋጠው ስለሚገኙ ከፍርስራሿ ከተማ ንቅንቅ አልልም ብሏል።

"ቤተሰቦቼ ጋር አልፎ አልፎ በቪዲዮ ጥሪ እንገናኛለን፤ ይናፍቁኛል፤ ግን ደግሞ እኔ እንደምኖርበት ሰቆቃ ውስጥ ባለመሆናቸው እፎይታ ይሰማኛል" ይላል የነፍስ አድን ሰራተኛው ሌይት።

ሌይት ከቤተሰቦቹ በጥቃቱ ቅድሚያ የተነጠቀው በ2012 ትንሽ ወንድሙን ነበር። ይህም "የነጭ ሄልሜትስ" ተብለው የሚጠሩትን የሲቪል ፈቃደኛ ነፍስ አድን ሠራተኞች ጋር የመጀመሪያ ሥራውን እንዲጀምር ምክንያት ሆኖታል።

"ከዚያ በኋላ ብዙ ከባድ የአየር ጥቃቶች ነበሩ፤ እዚህ ያሉት ብዙ ሰዎች እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። እነዚህን ሰዎች ልረዳቸው የምችለው እኔ እንደሆንኩ ተሰማኝና በሥራው ቀጠልኩ። ይህ የነፍስ አድን ሥራም በወንድሜ ሞት የተሰማኝን ሃዘን እንድረሳ ትልቅ አስተዋጽዖ አበርክቶልኛል" በማለት ሌይት ከነፍስ አድን ሥራው ጋር ተስማምቶ የቀጠለበትን ምክንያት ያብራራል።

ሌይት በአንድ ወቅት አንዲት አዛውንት በአየር ጥቃት በተመቱ የግንቦች ፍርስራሾች ተቀብራ እያለቀሰች ይሰማታል። ነገር ግን የት እንደሆነች መለየት አልቻለም። በመሆኑም የተከመረውን ፍርስራሽ በባዶ እጁ ለሰዓታት በመቆፈር ሴትዮዋን ከነ ህይወቷ ያገኘበትን አጋጣሚ መቼም አይረሳውም።

በየቀኑ ቦንብ እንደዝናብ እየወረደ ከተሞችን እንዳልነበሩ በሚያደርግበት የሶሪያ ምድር ተጎጅዎችን ቆፍሮ ማውጣት ብዙም እንግዳ ነገር አይደለም። ሌይት በቅርቡም አንዲት የ9 ዓመት ታዳጊን ከሌሎች የነፍስ አድን ሠራተኞች ጋር በመሆን ቆፍረው በማውጣት ሕይወቷን መታደጋቸውን ያስታውሳል።

ሌይት የዘጠኝ አመቷን ታዳጊ ቆፍሮ ሲያወጣ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሌይት የዘጠኝ አመቷን ታዳጊ ቆፍሮ ሲያወጣ

በቅርቡ ሌይት ዩኒቨርሲቲ አካባቢ በደረሰ ፍንዳታ፤ በፍንዳታው ጉዳት የደረሰባትን አንዲት ተማሪን ታቅፎ የሚያሳይ ምስል በስፋት ተዘዋውሯል። "ይህ ቅጽበት በጣም ትዝታ የሚያጭርና ምናልባትም መቼም የማልረሳው ነው" በማለት ሌይት ሁኔታውን ይገልጸዋል።

"ይህች ልጅ ተመራቂ ተማሪ ስትሆን በፍንዳታው ጉዳት ደርሶባት ነገር ግን በሕይወት ስለተገኘች ታቅፌያት ወደ ሆስፒታል ለመውሰድ አምቡላንስ እየተጠባበቅሁ ነበር። ግን አምቡላንሶቹ በጣም እየሞሉ ስለነበር እርሷን መጨመር አልቻሉም፤ እናም እጄ ላይ እያለች ሕይወቷ አለፈ።"

ከ2011 በፊት ሳራቄብ ዝነኛ የግብርና ምርት ማከፋፈያና ለደቡባዊ ኢድሊብ መንደሮች የትራንስፖርት እምብርት ነበረች።

ሌይት በአደጋው የተጎዳችን ልጅ ታቅፎ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሌይት በአደጋው የተጎዳችን ልጅ ታቅፎ

የደስታና የፌሽታ ከተማም ነበረች። በአጭሩ ሁሉም ነገር እንደአቅም የሚሸመትባት ልከኛ የሰው ልጅ መኖሪያ አድርገው ነዋሪዎቿ ይቆጥሯት ነበር። በፈረንጆቹ 2011 የተቀሰቀሰው የ'ርስበርስ ጦርነት ግን ይህን ነባራዊ ሁኔታ እንዳልነበር አድርጎታል።

አሁን የበሽር አላሳድ መንግሥት አካባቢውን መቆጣጠር ጀምሯል። ሌይትን ድብርት ውስጥ የከተተው የሺዎች መፈናቀል ሊመለስ ይችላል በሚል ተስፋውን እንደገና አለምልሞለታል።

የነፍስ አድን ሠራተኞች በነፍስ አድን ሥራ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የነፍስ አድን ሠራተኞች በነፍስ አድን ሥራ ላይ

"ከሳራቄብ መውጣት አልፈልግም፣ የእኔ ሕይወት እዚህ ነው፣ ሁሉም ነገሬ እዚህ ነው። በመጨረሻም ሁሉም ነገር እንደሚስተካከል ተስፋ አደርጋለሁ። ትልቁ ምኞቴም እሱ ነው" የሚለው ሌይት፤ የቦንብ ዝናብ መዝነቡ የትውልድ ከተማውን ለመልቀቅ አላስገደደውም። የመኖሬ ጥፍጥና የሚመጣው በሞት አፋፍ ላይ ያሉትን ወገኖቼን ወደ ህይወት መመለስ ነው፤ ከዚህ በላይ ደስታ የሚሰጠኝ ጉዳይ የለም ባይ ነው።