በትግራይ የወረዳነት ጥያቄ ባነሱ ነዋሪዎች የመቀሌ- ሳምረ መንገድ ከተዘጋ አራተኛ ቀኑን ይዟል

ነዋሪዎች በተቃውሞ ላይ

የፎቶው ባለመብት, FB

ታትሟል

ከመቀሌ ከተማ ወደ ሳምረ የሚወስደው መንገድ "ወረዳችን ይመለስልን" በሚሉ የሕንጣሎ ነዋሪዎች ደንጎላት በሚባል አካባቢ ከተዘጋ አራተኛ ቀኑን ይዟል።

'ሕንጣሎ ወጀራት' ተብሎ ይጠራ የነበረው ወረዳ ለሁለት ተከፍሎ፤ ወጀራት ራሱን የቻለ ወረዳ ሲሆን፤ 11 ጣቢያዎች ያሉት ሕንጣሎ ደግሞ ሒዋነ ከምትባል ሌላ ወረዳ ጋር እንዲካተት ተደርጓል።

ሒዋነ ከምትባለው ወረዳ ጋር እንዲቀላቀሉ የተደረጉት የሕንጣሎ ነዋሪች፤ እራሳችንን የቻለ ሕንጣሎ የተባለ ወረዳ ሊኖረን ይገባል እንጂ ከሒዋነ ወረዳ ጋር መቀላቀል የለብንም የሚል ቅሬታ ነው የሚያነሱት።

ከነዋሪዎቹ እንደሰማነው አሁን በተጀመረው አዲስ የአስተዳደር መዋቅር፤ ወጀራት ከ1-9 ጣቢያዎች ያሉት ሲሆን ሕንጣሎ ግን ሒዋነ ወደሚባል ወረዳ እንዲቀላቀል ተደርጓል።

ታዲያ ነዋሪዎቹ የራሳችን ወረዳ ይኑረን፤ በቅርብ አገልግሎት እንድናገኝ ይሁን በማለት ነው እየጠየቁ ያሉት።

"ምላሽ ካልተሰጠን ተቃውሟችን ይቀጥላል፤ ወደ ቤታችን አንመለስም" ይላሉ ነዋሪዎቹ።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪ "የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደብረጽዮን ባመጣው አዲስ አሠራር ፤ ነዋሪዎች ከ10 ኪሎሜትር በላይ ርቀው መገልገል የለባቸውም ሲሉ ነበር። እኛ ግን አሁን ተባረን አገልግሎት ለማግኘት የምንጓዘው ትንሹ ርቀት 30 ኪሎ ሜትር ነው" ይላሉ።

መንገድ መዝጋት መፍትሄ ነው ወይ? በማለት የተጠየቁት ነዋሪው፤ መንገድ መዝጋት ፍትሃዊ ባይሆንም ፍትህ ስላጣን ነው መንገድ የዘጋነው ብለዋል።

"ከእኛ መካከልም መቀሌ መሄድ ያለባት አራስ አለች፤ ሕመምተኛ አለ፤ ነገር ግን መሠረታዊ ሕይወታችን አደጋ ላይ ስለወደቀ ነው ይህንን ጊዜያዊ ችግራችንን ብንቋቋም ይሻላል ያልነው። ወረዳችንን አሳልፎ ለሌላ መስጠት ተገቢ አይደለም" ይላሉ።

የአካባቢው ነዋሪዎች ኮሚቴ ወኪል አቶ ደሱ ፀጋየም ይህንን ጥያቄ ማቅረብ ከጀመሩ ስድስት ወራት መቆጠራቸውን ይናገራሉ።

እርሳቸው እንደሚሉት ቅሬታቸውን ለማቅረብ ያልሄዱበት፤ ያልደረሱበት ቦታ የለም። በወረዳ እና በዞን የሚገኙ የፍትሕም ሆነ የፀጥታ አካላትን አዳርሰዋል። ነገር ግን ያገኙት ምላሽ የለም።

"እኛ መንግሥት በደነገገው ሕግ መሠረት ሁሉንም አሟልተናል። አንደኛ ከ115 ሺህ ሕዝብ በላይ ነን። ሁለተኛ መንግሥት 'ከ10 ኪሎ ሜትር በላይ ተጉዞ የወረዳ አገልግሎት ማግኘት የለበትም' ነው የሚለው እኛ ግን ከ30 በላይ ኪሎ ሜትር በላይ ሄደን ነው ይህንን አገልግሎት የምናገኘው፤ ስለዚህ የልማት ጥያቄያችን እንዲመለስልን ነው የምንፈልገው" ሲሉ ጥያቄያቸውን ለቢቢሲ አስረድተዋል።

ነገር ግን ይህንን ጥያቄ ማንሳት ከጀመሩ መንፈቅ ቢሞላቸውም፤ የፖለቲካ አስተዳዳሪዎችን መልስ እንዲሰጧቸው ቢጠይቁም ጆሮ የሰጣቸው የለም።

አቶ ደሱ "በተቃራኒው በዞንና በወረዳ ፖሊስ አማካኝነት ያስፈራሩን ገቡ፤ ለተቃውሞ የወጡ ነዋሪዎችም መንገድ በመዝጋታቸው ወደ ገበያ የሚሄዱ ከብቶች ሳይቀሩ መንገድ ላይ ነው የዋሉት፤ መንገድ ዝግ ነው፤ ይሄው እንዲህ ከሆነ ቀናት ተቆጥረዋል" ብለዋል።

ከአካባቢው ነዋሪዎች እንደሰማነው መንገዱ በመዘጋቱ ከትናንት በስቲያ እስከ 150 የሚደርሱ መኪኖች መንገድ ላይ ሲጉላሉ እንደነበር አስታውሰዋል።

የነዋሪዎቹን ጥያቄ ይዘን ምላሽ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል አማካሪ አቶ ተሾመ፤ የነዋሪዎቹ ጥያቄ እንደተመለሰላቸው ተናግረዋል።

አቶ ተሾመ "ወረዳቸው ተመልሶላቸዋል፤ የእነርሱ ጥያቄ የወረዳው ዋና ከተማ ደንጎላት ትሁን ወይስ ሒዋነ የሚል ነው" በማለት ይህንን ጥያቄ የሚመልሰው ደግሞ የወረዳው ምክር ቤት መሆኑን አስረድተዋል።

ጥያቄያቸው አልተመለሰልንም የሚሉት ነዋሪዎች፤ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እንዲያነጋግሯቸው ነው የሚፈልጉት ይህ ለምን አልሆነም? ያልናቸው አቶ ተሾመ፤ "ዝም ተብሎ የሚመጣበት ቦታ አይደለም፤ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በሌላ ሥራ ተጠምደዋል፤ በቀጠሮ ከመጣችሁ ትስተናገዳላችሁ አልናቸው። እንዴት እናድርግ? "ይላሉ።

ነዋሪዎች ግን መስተዳደሩ ጋር ጭራሽኑ አናገናኛችሁም መባላቸውን ያነሳንላቸው አቶ ተሾመ፤ ራሳቸው እንዳነጋገሯቸው በመግለፅ ይህ ሀሰት መሆኑን ገልፀዋል።