ጎንደር የጥምቀት በዓልን ለማክበር እንዴት እየተዘጋጀች ነው?

የፎቶው ባለመብት, J. Countess
የጥምቀት በዓል በድምቀት ከሚከበርባቸው ከተሞች መካከል ጎንደር ተጠቃሽ ነች።
ለበዓሉ ዝግጅት የሚጀመረውም ቀደም ተብሎ ነው። በዘንድሮው ደግሞ ከሃይማኖታዊ ክብረ በዓል በተጨማሪ ሌሎች ባህልንና ታሪክን የሚያስተዋውቁ ትዕይንቶችም እንደተዘጋጁ ተነግሯል።
በዓሉን በተለያየ ቦታ የማክበር አጋጣሚ የነበረው ኤርሚያስ ዘመነ፤ በጎንደር ሲያከብር ግን የተለየ ስሜት እንደሚሰማው ይናገራል። "በሌሎች ከተሞች ከሚከበረውም ለየት ይላል" ይላል።
"ታቦታቱ በጠቅላላ በአንድ ሥፍራ ማረፋቸው፣ በፋሲለደስ መዋኛ ገንዳ መከበሩ፤ ምዕመናኑም እየዋኙ የሚጠመቁበት፤ ከገንዳው ዳር ላይ የቆሙ ቀሳውስት ካባ ለብሰው ፀበሉን የመባረክ ሥነ ሥርዓቱ፣ ዝማሬው፣ አልባሳትና ትዕይንት መቼም ከአዕምሮዬ አይጠፋም" ሲል ስለ በዓሉ ድምቀት ይናገራል።
የዘንድሮውን የጥምቀት በዓል ለማክበርም ጎንደር የገባው ቀደም ብሎ ነው፤ ለበዓሉም ጃኖ አሰፍቶ ተሰናድቷል።
ከተማው እየተፀዳ፤ እየተጌጠ ነው። ከጎንደር ዙሪያ ካሉ አካባቢዎች የመጡ የባህል ቡድኖች ከተማው ገብተዋል።
ኤርሚያስ እንደነገረን ጎንደር ጥር 6 ቀን የአፄ ቴዎድሮስን ልደት ካከበሩ በኋላ የጥምቀት ዋዜማ ሆኖ መከበር ይጀመራል። እለቱም በተለያዩ ትዕይንቶች ተከብሮ ይውላል።
"ከተማዋ ሞቅ ደመቅ እንዳለች ነው፤ በርካታ ጎብኝዎችም ወደ ከተማዋ እየገቡ ነው፤ ካፍቴሪያም ሆነ ሆቴሎች ላይ ጎብኝዎች በርከት ብለው ይታያሉ" የሚለው ኤርሚያስ፤ የባህል ልብሶች መሸጫ አካባቢዎችም በጣም የተጨናነቁ ናቸው ብሎናል።

የፎቶው ባለመብት, Ermias Zerihun
የጎንደር ከተማ ባህል ቱሪዝም የባህል ኢንዱስትሪ ልማት ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ልዕልና ገ/መስቀል በፊታችን በሚከበረው የጥምቀት በዓል ወቅት ታሪክንና ባህልን የሚያጎሉ ተግባራትን በማከናወን ለጎብኝዎች ለማቅረብ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
የጥምቀት በዓል አከባበር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየደመቀ መምጣቱን የሚናገሩት አቶ ልዕልና፤ በዚህ ወቅት ወደ ከተማዋ የሚገቡ ጎብኝዎች ቁጥርም እየጨመረ እንደሆነ አስረድተዋል።
ወደ 30 ሺህ የሚጠጉ የውጭ ጎብኝዎችም ጎንደር ይገባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ነግረውናል።
'የነገሥታቱን ታሪክ የሚያሳይ ወካይ ትዕይንት'
አቶ ልዕልና እንደገለፁልን ቢያንስ በሳምንት ሁለት ቀን፤ ሐሙስና ቅዳሜ የነገሥታት እራት ይዘጋጃል።
በበዓሉ ወቅት ለእራቱ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ይጋበዛሉ። ይህ ዝግጅት ቀጣይነት ያለው ሲሆን፤ ጎብኝዎች ታሪካዊ የሆነውን ቤተ መንግሥት ከጎበኙ በኋላ እራቱን በክፍያ እንዲመገቡ ይሆናል።
ባህልና ቱሪዝም ከሌሎች ጋር በመተባባር ምግብና መጠጡን ያቀርባሉ። ይህም ለቱሪዝሙ ተጨማሪ ገቢ እንደሚያስገኝ አስረድተዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ነገሥታቶቹ ምን ያከናውኑ ነበር?፣ እንዴት አገር ይመሩ ነበር?፣ ምን ዓይነት ባህል ነበራቸው? የሚለው የነገሥታቱ ወካይ ትዕይንት ይቀርባል። በዚህም ጎብኝዎች ስለጎንደር ታሪክና ባህል በቀላሉ እንዲረዱ የሚያስችላቸውን አጋጣሚ ይፈጥርላቸዋል ብለዋል- አቶ ልዕልና።
በጎንደር አካባቢ ተፈጥረው የነበሩት የፀጥታ ችግሮች በቱሪዝሙ ላይ ያሳደሩት አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳለ የጠየቅናቸው አቶ ልዕልና፤ እዚህ ግባ የሚባል ተፅእኖ አለማድረሱን ገልፀውልናል።
በዘንድሮው ዓመት በአጠቃላይ 2 ሚሊየን ሕዝብ በዓሉን ያከብራሉ ተብሎም ይጠበቃል ይላሉ።
በተለያዩ የአገሪቷ ክፍል ያሉ ከተሞች ተወካዮች እንዲገኙም እየተደረገ ነው የሚሉት አቶ ልዕልና፤ ከጋሞ ተነስተው በሚመጡ አባቶችና ታዋቂ ግለሰቦች በበዓሉ እንዲታደሙና በጋራ ኢትዮጵያዊ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ ቃል የሚገቡበት በዓል እንዲሆን ግብዣ መደረጉን አክለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Prime Minister Office
ያነጋገርናቸው የጎንደር ከተማ ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር እንየው፤ በዓሉን በሰላም ለማክበር እቅድ ተዘጋጅቶ ለሚመለከታቸው አካላት መመሪያ ተሰጥቷቸው ወደ ሥራ መግባታቸውን ነግረውናል።
ከዚህ ቀደም በጎንደር ዙሪያ አካባቢዎች የተፈጠሩ የፀጥታ ችግሮች መኖራቸውን ያስታወሱት ኮማንደሩ፤ አሁን ላይ ያለው የፀጥታ ሁኔታ አስተማማኝ መሆኑን ገልፀዋል።
የፀጥታ ሁኔታውን ለማስከበርም ወጣቶች እና የሃይማኖት አባቶችን ጨምሮ በየደረጃው ያሉ የፀጥታ አካላት ተሰማርተው እንደሚገኙ አክለዋል።
በዓሉን አስመልክቶ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ጎንደር 19 ተጨማሪ በረራዎችን ማዘጋጀቱን አስታውቋል።
የጥምቀት ክብረ በዓል በሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ ሆኖ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) መመዝገቡ ይታወቃል።














