ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሰደድ እሳቱን ለመቆጣጠር የአውስትራሊያ ጦር ጥሪ ቀረበለት
የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚንስትር ስኮት ሞሪሰን 3000 ተጠባባቂ ወታደሮች የሰደድ እሳቱን ለመቆጣጠር እንደሚሰማሩ አስታወቁ።
የመከላከያ ሚንስትር ሊንዳ ሬይኖለደስ በበኩላቸው ወታደሮች የሰደድ እሳት ለማስቆም ጥሪ ሲቀርብላቸው ይህ በአውስትራሊያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ብለዋል።
በደቡብ ምስራቅ አውስትራሊያ የሙቀት መጠኑ ከ40 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ ሆኗል።
ባለሥልጣናት ቅዳሜ ለአውስትራሊያዊያን ''አደገኛ ቀን'' ሊሆን ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
የሰደድ እሳቱ ከተነሳ ከመስከርም ወር ጀምሮ እስካሁን 23 ሰዎች መሞታቸው ሲረጋገጥ፤ በርካቶች የደረሱበት አልታወቀም። 1500 በላይ ቤቶችም በእሳቱ ሙሉ ለሙሉ ወድመዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ሞሪሰን ለጋዜጠኞች ሲናገሩ፤ የሰደድ እሳቱ ተባብሶ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሷል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚንስትሩ ሰደድ እሳት ተዋጊ የሆኑ ተጨማሪ አውሮፕላኖችንም ወደ ሥራ ለማስገባት ተጨማሪ በጀት መጽደቁን ተናግረዋል።
በአውስትራሊያ በተለይ ደግሞ ደቡብ ምስራቁ ክፍል ላይ እየተስተዋለ ያለው ከባድ ሙቀት ከኃይለኛ ንፋስ ጋር ተደማምሮ የሰደድ እሳቱን መቆጣጠር አዳጋች አድርጎታል።
ከባድ ሙቀት ከየትኛው ተፈጥሯዊ ሞት በበለጠ በአውስትራሊያ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች ሞት ምክንያት ነው።
ለዚህ ሁሉ መከራ መነሻው የሕንድ ውቅያኖስ ዲፖሌ (IOD) ሚቲዮሮሎጂካዊ ክስተት ሲሆን ውቅያኖሱን በሚጎራበቱና በምድር ወገብ አቅራቢያ ባሉ ሀገራት የዝናብ ሁኔታን ይቀይራል።
ይህም ከምስራቅ አፍሪካ እስከ ኢንዶኔዥያ ድረስ የተለጠጠ ሲሆን የአየር ጠባዩ እስከ አውስትራሊያ ድረስ ርቆ ይስተዋላል።
በአውስትራሊያ ከባድ ድርቅ እና ሰደድ እሳት ሊከሰት እንደሚችል መረጃው ቢደርሳትም ምንም ማድረግ አልቻለችም።