በሜክሲኮ እስር ቤት ውስጥ በተቀሰቀሰ ግጭት 16 ሰዎች ሞቱ

በሞንተሪ የሚገኘው እና በቅርቡ የተዘጋው ቶፖ ችኮ እስር ቤት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, በሜክሲኮ ሙስና በተንሰራፋባቸው እና በተጨናነቁ እስር ቤቶች ግጭቶች መከሰታቸው የተለመደ ነው
ታትሟል

በማዕከላዊ ሜክሲኮ በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ በተነሳ ግጭት ቢያንስ 16 እስረኞች መሞታቸውን ባለሥልጣናት ተናገሩ። በዛካቴካስ ግዛት ሲየንጉላስ ከተማ በሚገኝ እስር ቤት በተነሳው በዚሁ ግጭት ሌሎች 5 እስረኞችም ለጉዳት ተዳርገዋል።

በግጭቱ 15ቱ እስረኞች በዚያው በእስር ቤት ውስጥ እያሉ የሞቱ ሲሆን አንደኛው ሆስፒታል ከደረሰ በኋላ ሕይወቱ አልፏል።

የዛካቴካስ ግዛት ደህንነት ፀሐፊ ኢስማኤል ካምቤሮስ ሄርናንዴዝ፤ ለአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን እንደገለፁት፤ አንዳንዶቹ ተጎጅዎች በጥይት የተመቱ ሲሆን ሌሎች ደግሞ በተለያዩ ስለታማ ነገሮች ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው።

ባለሥልጣናቱ እንዳሉት፤ ለ2 ሰዓት ከግማሽ ያህል በዘለቀው በዚህ ግጭት እስረኞቹ ሽጉጦችንና ቢላዎችን በመጠቀም እርስ በርስ ሲደባደቡ ነበር።

በሜክሲኮ እስር ቤቶች በተለይ በጣም በተጨናነቁ እና እፅ ተጠቃሚ ወንበዴዎች ባሉባቸው እስር ቤቶች እንዲህ ዓይነት ግጭት ሲያጋጥም ይህ አዲስ አይደለም።

የግዛቷ የደህንነት ኤጀንሲ እንዳለው፤ ግጭቱ በሲየንጉላስ ባለፈው ማክሰኞ ምሽት 2፡30 ላይ ተቀስቅሶ በቁጥጥር ሥር የዋለው ለሁለት ሰዓት ከግማሽ በላይ ከዘለቀ በኋላ ነበር።

አንድ እስረኛ ከያዘው መሣሪያ ጋር በቁጥጥር ሥር የዋለ ሲሆን፤ ሌሎች ሽጉጦችና ቢላዎችም በእስር ቤት ውስጥ ተገኝተዋል።

በግጭቱ በእስር ቤት ጠባቂዎችም ሆነ ፖሊስ ላይ የደረሰ ጉዳት የለም።

ግጭቱ እንዴት እንደተጀመረ እስካሁን በግልፅ ታወቀ ነገር የለም። የአገሪቷ መንግሥት ግጭቱን ማን እንደቀሰቀሰውና መሣሪያዎቹ ወደ እስር ቤት እንዴት እንደገቡ ምርመራ እየተካሄደ እንደሆነ ገልጿል።

በሜክሲኮ ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ፤ በሞርሎስ ማዕከላዊ ግዛት እስር ቤት በተነሳ ግጭት ስድስት ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።