በፓናማ እስር ቤት አደገኛ ቦዘኔዎች ሲታኮሱ ዋሉ፤ 13ቱ ተገድለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ዛሬ በፖናማ እስር ቤት ከፍተኛ የተኩስ ልውውጥ ሲደረግ ነበር። 13 እስረኞች ወዲያውኑ የሞቱ ሲሆን 15 የሚሆኑት ክፉኛ ቆስለዋል።
የፓናማ ባለሥልጣናት በእስረኞቹ እጅ 'ኤኬ 47' የጦር መሣሪያ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ላውረንቲኖ ኮርቲዞ ምርመራ እንደሚጀመር ቃል ገብተዋል።
ብዙዎችን ባለሥልጣናት ያስገረማቸው እንዴት እነዚህ የጦር መሣሪያዎች በእስረኞች እጅ ሊገቡ ቻሉ? እስከዛሬስ የት ደብቀዋቸው ነበር የሚለው ነው።
"መቼም ከሰማይ ዱብ አላሉ፤ አንዳች የተቀናጀ የመሣሪያ ሽያጭ በዚያ እስር ቤት ውስጥ ሲካሄድ እንደነበር ጥርጥር የለውም" ብለዋል ፕሬዝዳንት ኮርቲዞ።
ፕሬዝዳንቱ ጨምረው እንዳሉት ዛሬ ረቡዕ የጸጥታና ደህንነት ኃላፊዎቻቸውን ሰብስበው በጉዳዩ ላይ ይነጋገሩበታል።
"ይህ ነገር የሆነ ቦታ መቆም አለበት፤ በቅርቡ በእስር ቤቶች ውስጥ ፍተሻ አድርገን የተወሰኑ የጦር መሣሪዎችን አግኝተን ነበር፤ የጦር መሣሪያ እንዴት ወደ እስር ቤት እንደሚገባ ሳናውቅ እንቅልፍ የለንም" ብለዋል።
ላ ጆይቶ በሚባለው እስር ቤት በታሳሪዎች መካከል የተኩስ ልውውጡ የጀመረው ከሰዓት 8፡00 ሰዓት ላይ ነበር። ይህ እስር ቤት የሚገኘው በዋና ከተማዋ በፓናማ ሲቲ ምሥራቃዊ ክፍል ነው።
የፓናማ ፖሊስ ረዳት አዛዥ አሌክሲስ ሞኖዝ እንደተናገሩት ከሆነ የተኩስ ልውውጡ በአንድ አደገኛ ቦዘኔ ቡድን አባላት መካከል በተነሳ አለመግባባት የተጀመረ ነው።
ምንም እንኳ ላ ጆይታ እስር ቤት የታሰሩ ቁጥር ሥፍር ባይኖራቸውም፣ ይህ የአደገኛ ቦዘኔዎችን የቀጠፈው ዓይነት የተኩስ ልውውጥ ግን በቅርብ ጊዜ ታይቶም ተሰምቶም የማይታወቅ ነው።
በመካከለኛው አሜሪካ በምትገኘው ፓናማ በደረሰው በዚህ የመገዳደል ተግባር መሀል ታዲያ አንድም ያመለጠ እስረኛ የለም።













