አሜሪካ፡ 50 ዶላር የሰረቀው ግለሰብ ከ36 ዓመታት እስር በኋላ ነፃ ወጣ

አልቪን ኬናርድ ፍርድ ቤት ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, CBS

የምስሉ መግለጫ, አልቪን ኬናርድ ወጣትነቱን ያሳለፈው በእስር ቤት ነው
ታትሟል

ከዳቦ ጋጋሪ 50 ዶላር (1450 ብር ገደማ) በመስረቅ ዕድሜ ይፍታህ ተፈርዶበት የነበረውን ግለሰብ የአላባማ ፍርድ ቤት ከ36 ዓመታት እስር በኋላ ነፃ እንዲወጣ ወስኗል። የ58 ዓመቱ ጎልማሳ አልቪን ኬናደርድ በአውሮፓዊያኑ 1970 በወጣው ሕግ መሠረት ውሳኔው ተላልፎበታል።

ፍርዱ ኬናርድን በእስር ቤት ቆይታው ሁሉ ለመጠየቅ የሚሄዱ ቤተሰቦችና ወዳጆችን ስሜት የነካና እጅግ ያስቆጣ ነበር።

የግለሰቡ ጠበቃ ካርላ ክራውደር፤ ግለሰቡ ከሦስት አስርት ዓመታት በኋላ ይህንን እድል በማግኘቱ ተደስቷል፤ ከቤተሰቦቹ ጋር ለመቀላቀልም ጓጉቷል ብላለች። ከዚህ ቀደም ይሠራው ወደነበረው የእንጨት ሥራ ለመመለስ እንደሚፈልግም አክላለች።

ኬናርድ የ22 ዓመት ወጣት ሳለ አንድ ዳቦ ጋጋሪን በቢላ በማስፈራራት ዘርፏል ተብሎ ነበር እስር የተፈረደበት፤ ይሁን እንጂ በግለሰቡ ላይ ምንም አይነት ጉዳት አላደረሰም።

በዚህም ምክንያት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የእድሜ ልክ እስራት ተበይኖበታል።

ግለሰቡ ከዚህ ቀደም ወደ አንድ ህንፃ በሕገ ወጥ መንገድ ለዘረፋ ገብተሃል በሚል ጥፋተኛ ከመባሉ በስተቀር ሌላ የቀረበበት ክስ አልነበረም።

ኬናርድ የእስረኛ ልብሱን እንደለበሰ ለድርጊቶቹ ሁሉ ተጠያቂ እንደሆነ እና ሙሉ ኃላፊነቱን እንደሚወስድ ለዳኛው አስረድቷል። በዚህ ጊዜ ቤተሰቦቹና ወዳጆቹ በደስታ ዘለሉ። ከእስር ነፃ መባሉን ሲሰሙም አቀፉት፤ በደስታ ፈነጠዙ።

"ሁላችንም አለቀስን" ትላለች የእህቱ ልጅ ፓትሪሺያ። ከ20 ለሚበልጡ ዓመታት ስለመፈታቱ ያወራ ነበር ስትል ጨምራም ተናግራለች።

ክራውደር ለ 'ዘ ጋርዲያን' እንደገለፀችው ግለሰቡ እድሜ ይፍታህ ሲበየንበት እንኳን ሕይወቱ እንደሚለወጥ ያስብ ነበር።

እርሷ እንደምትለው በእስር ቤት ውስጥ የደረሰበትን በደል "አንድ ሰው እስር ቤት ውስጥ ገብቶ ቢያየው፤ በዚህ ክረምት እንዴት እንደሚሞቅ ያይ ነበር" ሲል በእስር ቤቱ ውስጥ መሠረታዊ ነገሮች እንዳልነበሩ በስላቅ ተናግሯል።