በደቡብ አፍሪካ የመፀዳጃ ቤት ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ ለሞተው ታዳጊ ካሳ እንዲከፈል ተወሰነ

ማይክል ኮማፔ

የፎቶው ባለመብት, Supplied by Komape family

ታትሟል

የደቡብ አፍሪካ ፍርድ ቤት የመፀዳጃ ቤት ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ ለሞተው ታዳጊ ወላጆች ካሳ እንዲከፈል ወሰነ።

የአምስት ዓመቱ ታዳጊ ማይክል ኮማፔ በሚማርበት ትምህርት ቤት በሚገኘው መፀዳጃ ቤት ጉድጓድ ውስጥ ነበር ገብቶ የሞተው።

ምንም እንኳን የሃገሪቱ መሠረታዊ የትምህርት ጉዳዮች ሚንስቴር ለታዳጊው ሞት ኃላፊነቱን አልወስድም ቢልም፤ የፍርድ ቤቱ ዳኛ የመሠረታዊ ትምህርት ክፍል ቢሮ ለታዳጊው ወላጆች 1 ሚሊዮን የደቡብ አፍሪካ ራንድ (2.1 ሚሊዮን ብር) በካሳ መልክ እንዲከፈል በይነዋል።

ማይክል እአአ 2014 ነበር ከመማሪያ ክፍሉ ወጥቶ ወደ መፀዳጃ ቤት ሄዶ ሳይመለስ የቀረው።

የታዳጊው ሞት በደቡብ አፍሪካ ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሶ የነበረ ሲሆን፤ በትምህርት ቤቶች ውስጥ በቂ እና ደረጃቸውን የጠበቁ መጸዳጃ ቤቶች የሉም ሲሉ በርካቶች ሲተቹ ቆይተዋል።

የማይክል ወላጆች ጄምስ እና ሮሲና ለልጃቸው ሞት የመሠረታዊ ትምህርት ሚንስቴርን ተጠያቂ ያደርጋሉ።

በደቡብ አፍሪካ ከሚገኙ 25ሺህ ትምህርት ቤቶች መካከል ከ4ሺህ በላይ የሚሆኑት በውስጣቸው የያዙት ባለ ጉድጓድ (የቁጢጥ) መፀዳጃ ቤት ነው። ይህም የተማሪዎችን ደህንነት አደጋ ላይ የሚጥል ነው ተብሏል።

በተመሳሳይ መልኩ ከአንድ ዓመት በፊት ሌላ የአምስት ዓመት ታዳጊ መፀዳጃ ቤት ጉድጓድ ውስጥ ገብቶ ነበር።

ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ ሃገራቸው ደቡብ አፍሪካ በሁለት ዓመታት ውስጥ በመላው ትምህርት ቤቶች ውስጥ የጉድጓድ መፀዳጃ ቤቶችን እንደምታስወግድ ቃል ገብተው ነበር።