ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከጎጃም እናቶች አንገት ላይ ስለማይታጣው ማርትሬዛ ምን ያክል ያውቃሉ?
በኢትዮጵያ በተለይ ደግሞ የጎጃም እናቶች አንገታቸው ላይ ለመዋቢያነት የሚያደርጉት 'ማርትሬዛ' ወይም 'ጠገራ' ተብሎ የሚጠራው ሳንቲም ምንጩ ከወዴት እንደሆነ ጠይቀው ያውቃሉ?
ከየት መጣ? እንዴት መጣ? እንዴትስ ለመዋቢያነት ጥቅም ላይ ዋለ?
ጠገራውን ለመዋቢያነት ከአንገቷ ላይ አኑራ በባህር ዳር ከተማ ገብያ መሃል ያገኘናት ወ/ሮ እሙዬ ጓዴ "በባህላችን ሴት ልጅ ስትዳር ይሄ ይሰጣታል። ለእርሷ የሚቀርባት ሰው ነው የሚሰጣት። ይሄ የቀድሞ ጠገራ ነው፤ የትም አይገኝም" ትላለች።
ወ/ሮ እሙዬ ጠገራው ከየት እንደመጣ እርግጠኛ ባይሆኑም፤ ከቀደመ ትውልድ እንደወረሱት ይናገራሉ። "ጠገራው የአያቴ ነበር። አያቴ ለእናቴ ሰጠቻት። እናቴ ደግሞ ለእኔ ሰጠችኝ። አሁን አንገቴ ላይ ካኖርኩት ከ40 ዓመት በላይ ይሆነዋለ" ብላለች።
"የሃገር ባህል ነው። ሴቶች ሲዳሩ እንደ ጥሎሽ ነበር የሚሰጣቸው። ጠገራው ከብር ስለሚሰራ ብዙ ገንዘብ ያወጣል። ስለሚያምር ለመዋቢያነት ይውላል" የሚሉት ደግሞ እዚያው ገብያ መሃል ያገኘናቸው አቶ አማረ ናቸው።
ማርትሬዛ ወይም ጠገራ ከየት መጣ?
ሙሉ መጠሪያው ማሪያ ቴሬሳ ቴለር ሲሆን ለመገበያያነት ጥቅም ላይ ይውል የነበረ ሳንቲም ነው።
መጠሪያውን ያገኘው ከኦስትሪያ-ሃነጋሪ ንግስት ስም ማሪያ ቴሬዛ ታለር ነው።
ይህ ለመገበያያነት ይውል የነበረው ሳንቲም በአውሮፓዊቷ ሃገረ ኦስትሪያ ከ1730ዎቹ እስከ 1770ዎቹ ድረስ ባሉት የማሪያ ቴሬዛ ታለር ንግስና ዓመታት ታትሟል።
ማሪያ ቴሬሳ ቴለር በዓለም ላይ በስፋት ከሚታወቁት መገበያያ ሳንቲሞች መካከል አንዱ የነበረ ሲሆን፤ የአረብ ሃገራት ነጋዴዎች ከአውሮፓ ሃገራት ጋር ለሚያደርጉት ግብይት የሚቀበሉት ማሪያ ቴሬሳ ቴለርን ብቻ ስለመሆኑ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።
ማሪያ ቴሬሳ ቴለር ሳንቲም ወደ ኢትዮጵያ እንዴት ገባ?
በአማራ ክልል ባህል እና ቱሪዝም ቢሮ የታሪክ ጥናት ባለሙያ የሆኑት አቶ ዳምጤ ደምሴ፤ ''ማርትሬዛ በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች ወደ ኢትዮጵያ ገብቷል" ይላሉ።
አቶ ዳምጤ "የጎንደሩ ዳግማዊ አጼ እያሱ የንግስና ዘመን ማብቂያ አካባቢ ሳንቲሙ ወደ ኢትዮጵያ ሲገባ ነበር። ነጋዴዎች፣ አውሮፓውያን አሳሾች እና ተጓዦች ወደ ሃገራችን ይዘውት መጥተዋል" ብለውናል።
ክርስቲያን ጎቲች የተባሉ ክሮሺያዊ የታሪክ ተመራማሪ ''ዘ ቴለር ኦፍ ማሪያ ቴሬዛ'' በተሰኘው ጽሁፋቸው፤ በአውሮፓ በተለይ ደግሞ በቪዬና ከተማ ከተቀረጹ 245 ሚሊዮን ከሚሆኑት ማሪያ ቴሬሳ ቴለር ሳንቲሞች መካከል 20 በመቶ ያክሉ ወደ ኢትዮጵያ ስለመወሰዳቸው አትተዋል።
ይህ ሳንቲም ደግሞ በስፋት ወደ ኢትዮጵያ የገባው፤ በአጼ ቴዎድሮስ II ወቅት ወራሪው የእግሊዝ ጦር በፊልድ ማርሻል ሮቤርት ናፒየር እየተመራ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ፤ ለጉልበት ሥራ ለሚያሰማራቸው ሰዎች በክፍያ መልክ ይህን የጠገራ ሳንቲም ለመክፈል በብዛት ይዞ በመምጣቱ እንደሆነ ሪቻርድ ፓንክረስት ''ዘ ማሪያ ቴሬሳ ዶላር ኢን ፕሪ-ዋር ኢትዮጵያ'' በተሰኘው ጥናታዊ ጽሁፋቸው ላይ ጠቅሰዋል።
ከኢትዮጵያ በተጨማሪ በአውሮፓ እና መካከለኛው ምስራቅ ሃገራት ውስጥ ይህ ሳንቲም በስፋት እንደሚገኝ ይነገራል።
ዛሬ ላይ ማርትሬዛ ስንት ያወጣል
ከብር የተቀረጹት እኚህ ሳንቲሞች በኢንተርኔት ገበያዎች ላይ በመጠን እና በተቀረጹበት ዓመት ልዩነት መሰረት ከ15 እስከ 500 የአሜሪካ ዶላር ይሸጣሉ።
በኢትዮጵያም ከብር የተሰሩ ጠገራዎች እስከ 1500 ብር ይጠየቅባቸዋል።