ሩሲያ በወሰደችው አጸፋዊ እርምጃ የጀርመን አምባሳደሮችን አባረረች

የፎቶው ባለመብት, AFP
ጀርመን ከአንድ ሳምንት በፊት ለወሰደችው እርምጃ አጸፋ ለመስጠት በሚመስል መልኩ ሩሲያ ሁለት የበርሊን ዲፕሎማቶችን ከሃገሯ አባረረች።
ከወራት በፊት በበርሊን የሕዝብ ፓርክ ውስጥ ለተፈጸመው ግድያ ትዕዛዙ የተሰጠው በሩሲያ ሳይሆን አይቀርም በማለት ጀርመን መቀመጫቸውን በርሊን አድርገው የነበሩ ሁለት የሩሲያ አምባሳደሮችን ማባረሯ ይታወሳል።
የሩሲያ መንግሥት የተለመደ የዲፕሎማሲ ሥርዓትን እየተከተልኩ ነው ባለው እርምጃ፤ ሁለት የጀርመን አምባሳደሮችን አባሯል።
ከአራት ወራት በፊት የቀድሞ የቺቺኒያ አማጺያን ኮማንደር የነበረው የ40 ዓመቱ ጎልማሳ ዜሊምካሃን ክሃንጎሽቪሊ በርሊን ከተማ በሚገኝ ፓርክ ውስጥ እንዳለ ነበር ከጀርባ በኩል ጭንቅላቱን በጥይት ተትመቶ የተገደለው።
በወንጀሉ የተጠረጠረ አንድ የሩሲያ ዜጋ በበርሊን በቁጥጥር ሥር ውሎ ይገኛል።
በወቅቱ ከግድያው ጋር በተያያዘ ሁለቱ የሩሲያ አምባሳደሮቹ እንዲባረሩ መደረጉን እና ግድያው የተፈጸመው በሩሲያ መንግሥት ትዕዛዝ ሳይሆን አይቀርም መባሉን ሩሲያ አጥብቃ ኮንና ነበር።
ቭላድሚር ፑቲን ሰኞ ዕለት በፓርክ ውስጥ የተገደለውን ዜሊምካሃን ክሃንጎሽቪሊን ''ሽፍታ'' ብለው የጠሩት ሲሆን፤ የክሬምሊን መንግሥት ግን በግድያው እጁ እንደሌለበት ተናግረዋል።
አቃቤ ሕግ ተጠርጣሪው ግድያው ከመፈጸሙ ስድስት ቀናት በፊት ከሞስኮ ተነስቶ ወደ አውሮፓ እንደመጣ ተናግረዋል።
ግለሰቡን ሳይገድል አይቀርም ከተባለው ተጠርጣሪ የተገኘው መረጃ ግን አጥጋቢ አለመሆኑ ተነግሯል። ይሁን እንጂ አቃቤ ሕግ ከግድያው ጀርባ የሩሲያ ወይም የቺቺኒያ ሪፐብሊክ እጅ እንዳለ ማስረጃ አለኝ ይላል።
ሟቹ ዜሊምካሃን ክሃንጎሽቪሊ ማን ነበር?

የፎቶው ባለመብት, facebook
የጆርጂያ ዜግነት ያለው የ40 ዓመቱ ዜሊምካሃን ክሃንጎሽቪሊ፤ የቺቺኒያ አማጺያን ኮማንደር ሆኖ የሩሲያ ጦርን እአአ ከ2001-2005 ድረስ ተዋግቷል።
ዜሊምካሃን በሩሲያ ልዩ ኃይል የተገደሉት የቀድሞ የቺቺኒያ ፕሬዝደንት አስላን ማስካሃዶቭ የቅርብ አጋር ነበር።
የቀድሞ የአማጺያን ኮማንደሩ ዜሊምካሃን እአአ 2015 ላይ በትውልድ ሃገሩ ጆርጂያ መዲና ትብሊስ የግድያ ሙከራ ከተደረገበት በኋላ ነበር ወደ ጀርመን በማቅናት ጥገኝነት የጠየቀው፤ ምንም እንኳን የጥገኝነት ጥያቄው ከጀርመን መንግሥት ይሁንታ ባያገኝም።
ቺቺኒያ በአሁኑ ወቅት ለሩሲያ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ታማኝ በሆኑት ራመዛን ካድይሮቭ ትመራለች።












