በቼክ ሪፐብሊክ ሆስፒታል ስድስት ህመምተኞችን የገደለው ታጣቂ ራሱን አጠፋ

ቼክ ሪፐብሊካውያን ለሞቱት የተደረገ የሻማ ማብራት ስነ ስርዓት

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል

በቼክ ሪፐብሊኳ ከተማ ኦስትራቫ አንድ ግለሰብ በሆስፒታል ህመምተኞች መጠበቂያ ክፍል የነበሩ ስድስት ህመምተኞችን እንደገደለ ፖሊስ አስታውቋል።

ታጣቂው ከሶስት ሰዓታት በኋላም ራሱን በታጠቀው መሳሪያ አጥፍቷል ብሏል።

ታጣቂው በሆስፒታሉ ውስጥ ህመምተኛ ነበር የተባለ ሲሆን፤ ለምን እንደገደላቸው ግን የታወቀ ነገር የለም ተብሏል።

ፖሊሶች በቦታው ላይ በደረሱበት ወቅት ተጠርጣሪው ከአካባቢው ተሰውሮ እንደነበር ተገልጿል።

የሆስፒታሉ ዳይሬክተር ጂሪ ሃቭርናላንት ለቼክ ቴሌቪዥን እንደተናገሩት ታጣቂው ያለምንም ማስጠንቀቂያ የተኩስ እሩምታ የከፈተ ሲሆን ዘጠኝ ሰዎችም በሽጉጥ ተመትተዋል።

አራት ወንዶችና ሁለት ሴቶች ወዲያው የሞቱ ሲሆን ሶስቱ ደግሞ ክፉኛ ቆስለዋል፤ ሁሉም በሆስፒታሉ ውስጥ ህመምተኞች መሆናቸውም ተገልጿል።

ተኩሱን ተከትሎም ሆስፒታሉ አገልግሎት መስጠት አቋርጦ ሰራተኞቹ እንዳይገቡና እንዳይወጡ ተከልክለው ነበር።

ህመምተኞች ከሆስፒታል ሲወጡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

አንድ የአይን እማኝ ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት "ምን እንደተፈጠረ ለመናገር ይከብደኛል፤ በሆስፒታሉ ውስጥ በደም ክፍል ብሰራም፤ የደረሰው ነገር አሰቃቂ ነው፤ አሁንም በድንጋጤ ላይ ነኝ፤ መናገር ከምችለው በላይ አሳዝኖኛል።" ብለዋል።

ፖሊስ ታጣቂውን ለመፈለግ እርዳታን ሽቶ የነበረ ቢሆንም፤ ሰዎች ለደህንነታቸው ሲባል እንዳይጠጉት ከማስጠንቀቂያ ጋር ነው መልእክቱን ያስተላለፈው።

ተጣርጣሪው ከአባባቢው ተሰውሮ የነበረ ሲሆን፤ ፖሊስ የአርባ ሁለት አመቱን ታጣቂ ማንነት፣ ፎቶ ከሆስፒታሉ የደህንነት ካሜራዎች ማግኘት ከቻለ በኋላ በሄሊኮፕተር በመታገዝ ፍለጋውን አጠናክሮ ነበር። ሄሊኮፕተሩ በላይ እየበረረ እያለ ግለሰቡ ራሱን እንዳጠፋ ፖሊስ ገልጿል።

ተጠርጣሪው ግለሰብ

የፎቶው ባለመብት, Czech police handout

የተጠርጣሪው የስራ ባልደረቦች ለቼክ ሚዲያ እንደተናገሩት በጣም ታምሜያለሁ ብሎ እረፍት ወስዶ እንደነበር ነው። በስራው መሃንዲስም ነበር ብለዋል። ተጠርጣሪው ከመሞቱ በፊት እናቱን ሄዶ ጠይቆ ስላደረሰው ጥቃት እንደነገራት የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አንድሬጅ ባቢስ ገልፀዋል።

ምንም እንኳን በአደን ምክንያት ብዙ ሰዎች የጦር መሳሪያ ቢኖራቸውም እንዲህ አይነት ተኩሶች የተለመዱ እንዳልሆነ ተገልጿል።