ስፔን፡የህጻናት ፆታዊ ጥቃትን የሚደግፍ የዋትስአፕ ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር ዋሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የስፔን ፖሊስ በመላው ዓለም የሚገኙና የህጻናት ጾታዊ ጥቃትና ሌሎች ጭካኔ የተሞላባቸው ነገሮችን ሲፈጸምባቸው የሚያሳዩ ምስሎችንና ተንቀሳቃሽ ምስሎችን በዋትስአፕ የሚያጋሩና የሚደግፉ 33 ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታወቀ።
እነዚህ 33 ሰዎች የህፃናት ጥቃትን የሚያበረታታ የዋትስአፕ ቡድን አባላት ናቸው ተብሏል።
ለማየት እጅግ የሚዘገንኑና ሰላም የሚነሱ ምስሎችን የቡድኑ አባላት ይዝናኑበታል ሲል ገልጿል ፖሊስ።
በሶስት የተለያዩ አህጉራት ከሚገኙ 11 ሀገራት ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን 17ቱ ግን ከስፔን መሆናቸው ታውቋል። ስፔን ውስጥ ምርመራ ሲደረግባቸው ከነበሩት ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ ከ 18 ዓመት በታች ናቸው። ዝቅተኛው እድሜም የ 15 ዓመት ታዳጊ ነው ተብሏል።
ኡራጓይ ውስጥ ፖሊስ ሁለት ሰዎችን በቁጥጥር ስር ያዋለ ሲሆን አንደኛዋ ተጠርጣሪ ሴት ልጇ ላይ ጥቃት ስታደርስ የሚያሳዩ ምስሎችን ለዋትስአፕ ቡድኑ ታጋራ ነበር ብሏል ፖሊስ።
አንድ የ29 ዓመት ግሰለብ ደግሞ በቡድኑ የሚላኩ ፎቶዎችን በስልኩ ላይ በማስቀረትና ሌሎች የቡድኑ አባላት ታዳጊ ሴቶችን በመቅረብ ተመሳሳይ ምስሎችን እንዲልኩ በማበረታታት በሚል በቁጥጥር ስር ውሏል።
ግለሰቡ በተጨማሪም የቡድኑ አባላት ወደ ፖሊስ መሄድ የማይችሉ ስደተኛ ህጻናት ላይ እንዲያተኩሩ መልእክት ያስተላልፍ ነበር።
ተጠርጣሪዎቹ እንዴት ተያዙ?
የስፔን ብሄራዊ ፖሊስ ይህንን ቡድን መከታተል ከጀመረ ሁለት ዓመት ሆኖታል፤ ምርመራውን የጀመረውም በደረሱት የኢሜልና ሌሎች ጥቆማዎችን ተከትሎ ነው።
ስራውን ለማከናወንም ዩሮፖል፣ ኢንተርፖል እንዲሁም የኢኳዶርና የኮስታሪካ ፖሊስ ተሳትፈዋል።
በዚህም በስፔን፣ ኡራጓይ፣ እንግሊዝ፣ ኦኳዶር፣ ኮስታሪካ፣ ፔሩ፣ ህንድ፣ ጣልያን፣ ፈረንሳይ፣ ፓኪስታን እና ሶሪያ ውስጥ የሚገኙ 33 የዋትስአፕ ቡድኑ አባላት በቁጥጥር ስር ውለዋል።












