የዘጠኝ አመቱ ሊቅ ከዩኒቨርስቲ ለመመረቅ ጥቂት ወራት ሲቀሩት አቋረጠ

ላውረንት ሲሞንስ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ታትሟል

ቤልጂየማዊው የህፃን ሊቅ በሆላንድ ከሚገኘው ዩኒቨርስቲ ሊመረቅ ጥቂት ወራት ቢቀሩትም ትምህርቱን እንዲያቋርጥ ሆኗል።

የዘጠኝ አመቱ ላውረንት ሲሞንስ ቤተሰቦች ትምህርቱን ሳያጠናቅቅ እንዲያቋርጥ አድርገውታል።

ለዚህም እንደምክንያትነት የሰጡት ከሁለት ሳምንታት በኋላ የአስር ዓመት ልደቱን ስለሚያከብር ከዚያ ቀድሞ እንዲመረቅ ቅድመ ሁኔታ በማስቀመጣቸውና ዩኒቨርስቲው እሱን ማሟላት ስላልቻለ ነው።

ቤተሰቦቹ በዓለም ከዩኒቨርስቲ በዘጠኝ አመቱ የተመረቀ የመጀመሪያው ህፃን እንዲሆንም ፍላጎታቸው ነበር። ነገር ግን የሚማርበት ዩኒቨርስቲ ኤይንድሆቨን ሁኔታው አስቸጋሪ እንደሆነና ላውረንት ብዙ ፈተናዎችም ገና እንደሚቀሩት አስታውቋል።

ዩኒቨርስቲው ምርቃቱ ከጥቂት ወራት በኋላ ይሁን ቢልም ቤተሰቦቹ አሻፈረኝ ብለው እንዲያቋርጥ አድርገውታል።

ላውረንት የሶስት አመት የኤሌክትሪካል ምህንድስናን ፕሮግራም በአስር ወራት እንዲያጠናቅቅና የልደቱም ቀን እንዲመረቅ ቀነ ገደብ አስቀምጠውለት ነበር።

ላውረንት፣ ሊዲያና አሌክሳንደር ሲሞንስ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የላውረንት አባት አሌክሳንደር ሲሞንስ ለሆላንድ ሚዲያ እንደተናገሩት ልጃቸው በሚያገኘው የሚዲያ አትኩሮት ዩኒቨርስቲው በከፍተኛ ሁኔታ እየተቻቸው እንደሆነ ገልፀዋል።

"በተደጋጋሚ ልጁ በሚያገኘው የሚዲያ አትኩሮት ጫና እያሳደርንበት እንደሆነ ተችተውናል። በዚህም ከቀጠልን የስነልቦና ምርመራ ሊያደርጉ እንደሚገደዱም ዩኒቨርስቲው አሳውቆናል" በማለት ለሆላንድ ጋዜጣ ደ ቮልክስራንት ተናግረዋል።

"ህፃን ጎበዝ እግር ኳስ ተጫዋች ቢሆን የሚዲያ አትኩሮቱ ጥሩ ነው ብለን ነው የምናስበው፤ ልጄ የተለዬ ችሎታ አለው። በሱ ታዲያ ቢኮራ ምንድነው ችግሩ?" ብለዋል።

ላውረንት ሲሞንስ በኢንስታግራም ገፃቸው ላይ ባለፈው ወር ዩኒቨርስቲው የላከላቸውን ኢሜይል ፎቶ በማንሳት አጋርተውታል።

ከኢሜይሉ መረዳት እንደሚቻለው በዚህ ወር ላይ መመረቅ እንደሚችል ነበር፤ ነገር ግን ዩኒቨርስቲው በቅርቡ ባወጣው መግለጫ "አስር አመት ከመሙላቱ በፊት ለመመረቅ በሚል መመረቂያ ቀኑን ብናጣድፈው ልጁም ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳረፍ ነው። ምንም እንኳን የተለየ ችሎታ ቢኖረውም የትምህርት ሁኔታውም ይጎዳል" በሚል አትቷል።