ስዊድን በጁሊያን አሳንጅ ላይ ስታደርግ የነበረውን ምርመራ አቋረጠች

ታትሟል

የስዊድን አቃብያነ ህግ ከአስገድዶ መድፈር ጋር በተያያዘ የዊኪሊክስ መስራች ጁሊያን አሳንጅ ላይ እያደረጉ የነበሩትን ምርመራ አቆሙ።

የቀረበበትን የአስገድዶ መድፈር ውንጀላ ያልተቀበለው ጁሊያን አሳንጅ እንደ አውሮፓውያኑ በ2012 በለንደኑ የኢኳዶር ኤምባሲ ገብቶ ጥገኝነት በመጠየቅና በኤምባሲው ለሰባት ዓመታት በመቆየት ለስዊድን ተላልፎ ከመሰጠት ራሱን አትርፏል።

ቢሆንም ግን የ48 ዓመቱ አውስትራሊያዊ አሳንጅ የዋስትና ሁኔታን በመጣስ ከስምንት ወራት በፊት ከኢኳዶር ኤምባሲ ተባርሯል።

ከዚያም የ50 ሳምንት እስር ተፈርዶበት በአሁኑ ወቅት በለንደኑ ቤልማርሽ እስር ቤት ይገኛል።

አሳንጅ የተወነጀለበትን አስገድዶ መድፈር እንደ አውሮፓውያኑ በ2010 ስዊድን ውስጥ ፈፅሞታል ነው የተባለው። በጉዳዩ ላይ እየተደረገ የነበረው ምርመራ 2017 ላይም ቆሞ የነበረ ሲሆን እንደገና እንደ አዲስ የተንቀሳቀሰው አሳንጅ ከኢኳዶር ኤምባሲ ሲባረር ነበር።

አሳንጅ ላይ እየተደረገ የነበረው ምርመራ እንዲቋረጥ ውሳኔ የሰጡት የጠቅላይ አቃቤ ህግ ምክትል ዳይሬክተር ኤቫ ማሪ ፐርሰን "እዚህ ውሳኔ ላይ የደረስነው የተባለው ነገር ከተፈጠረ ረዥም ጊዜያት በመሄዳቸው ያለው ማስረጃ እየደከመ በመምጣቱ ነው" ብለዋል።

ምክትል ዳይሬክተሯ ጨምረውም ተጎጅዋ ተፈጠረ ላለችው ነገር በተደጋጋሚ የሰጠችው ማብራሪያ ተአማኒ፣ ግልፅና ምንም የሚጣረስ ነጥብ የሌለው እንደሆነ አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

"ቢሆንም ግን አጠቃላይ ግምገማዬ ነባራዊ ማስረጃዎች በጊዜ ሂደት እየደከሙ ምርመራውን መቀጠል የማያስፈልግበት ጊዜ ላይ መደረሱን ነው" ብለዋል።