ጀርመናዊያን ህጻናት ኩሬ ውስጥ የተጣሉ ፈንጂዎችን በማግኔት አወጡ

ከኩሬው ውስጥ የተገኙት ፈንጂዎችንና ጥይቶች

የፎቶው ባለመብት, GERMAN POLICE

ታትሟል

ምሥራቃዊ የጀርመን ክፍል ውስጥ ያሉ ሦስት ህጻናት ከፍተኛ አቅም ያለውን ማግኔት በመጠቀም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት አንድ ኩሬ ውስጥ ተጥለው የነበሩ ፈንጂዎችንና ጥይቶችን ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው ማውጣታቸው አነጋጋሪ ሆኗል።

ህጻናቱ ሊፈነዱ የሚችሉትን የጦር መሳሪያዎችን ሆደርደረፍ ተብላ በምትታወቀው ከተማ አቅራቢያ ባገኙበት ጊዜ ፖሊስ ጠርተው አሳውቀዋል።

ይህንን ተከትሎም ፖሊስ አካባቢውን ዘግቶ ሌሎች ሰዎችም ተመሳሳይ የጦር መሳሪያዎችን ካገኙ ወዲያውኑ እንዲያሳውቁ ፖሊስ ለነዋሪዎች ጥሪ አቅርቦ ያገኙትንም ነገር እንዳይነኩ መክሯል።

ስለምን እነዚህ ፈንጂዎችና ጥይቶች በኩሬው ውስጥ ሊጣሉ እንደቻሉ የሚጠቁም ግልጽ ምክንያት አልተገኘም።

ጀርመን ውስጥ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ጥቅም ላይ የዋሉና ሳይፈነዱ የቀሩ ፈንጂዎችና ተተኳሾች ስለሚገኙ ነዋሪዎች ከመኖሪያ አካባቢያቸው እንዲርቁ በተደጋጋሚ ተደርገዋል።

ጀርመን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ ላይ በብሪታኒያ፣ በአሜሪካና በሶቪየት የጦር አውሮፕላኖች በከባድ ሁኔታ ድብደባ ተፈጽሞባት ስለነበረ በርካታ ያልፈነዱ የጦር መሳሪያዎች በመላዋ አገሪቱ ተበትነው እንደሚገኙ ይታመናል።

ህጻናቱ ያገኟቸውን ፈንጂዎች በድንገት በራሳቸው ጊዜ ሊፈነዱና አደጋ ሊያደርሱ ስለሚችሉ የቦንብ አስወጋጅ ባለሙያዎች በጥንቃቄ ሊያስወግዷቸው ይገባል ተብሏል።

እነዚህ ያልፈነዱ የጦር መሳሪያዎች በአብዛኛው የሚገኙት ግንባታ በሚካሄድባቸው ስፍራዎች እንደሆነም ተገልጿል።