የኢራቅ አለመረጋጋት፡ ተቃዋሚዎች በካርባላ የሚገኘው የኢራን ቆንስላ ላይ ጥቃት ሰነዘሩ

የኢራቅ ተቃዋሚዎች በካርባላ በሚገኘው የኢራን ቆንስላ አጥር ላይ ተቀጣጣይ ነገሮችን ሲወረውሩ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል

የኢራቅ ተቃዋሚዎች ትናንት ምሽት በኢራቅ ካርባላ በሚገኘው የኢራን ቆንስላ ላይ ጥቃት የሰነዘሩ ሲሆን ቢያንስ ሦስት ሰዎች መገደላቸው ተገልጿል።

ኢራን በኢራቅ ውስጣዊ ጉዳይ ላይ መግባቷን እንድታቆም የጠየቁት ተቃዋሚዎቹ በቆንስላው አጥር ላይ ተንጠላጥለው ታይተዋል።

ሪፖርቶች የፀጥታ ሠራተኞቹ በተቃዋሚዎቹ ላይ ተኩስ እንደከፈቱ ቢገልፅም፤ ሌሎች ደግሞ ማንነታቸው ያልታወቁ የታጠቁ ኃይሎች ተጠያቂ እንደሆኑ ገልፀዋል።

ሰኞ እለትም በባግዳድ ለተቃውሞ በተሰባሰቡ ሰዎች ላይ የፀጥታ ኃይሎች ተኩስ ከፍተው እንደነበር ሪፖርቶች አመልክተዋል።

የኢራቅ ጠቅላይ ሚኒስትር አደል አብዱል መሃዲ ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፤ በሀገሪቱ እየተካሄደ ያለው የተቃውሞ ሰልፍ ሀገሪቱን ወደ ኢኮኖሚ ቀውስ ሊያመራት እንደሚችል ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም መንግሥት ሰላማዊ የሆኑ ተቃውሞዎችን ቢያከብርም፤ በዋና መዲናዋ መንገድ መዝጋትና በደቡብ ካሉና ቁልፍ የሆኑ የነዳጅ መተላለፊያ ወደቦችን መዝጋት አገሪቷን በቢሊዮን የሚቆጠር ኪሳራ ውስጥ ሊከታት ይችላል፤ ይህም የዋጋ ጭማሪም እንደሚያስከትል ገልፀዋል።

ተቃዋሚዎች ማስተላለፍ የፈለጉትን መልዕክት በሚገባ ተረድተናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ከዚህ በኋላ የሚያሰሙትን ተቃውሞ በማቆም ሰላማዊ ሕይወታቸውን እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት ጠቅላይ ሚኒስተር አብዱል ማሀዲ የሚተካቸው ሰው ከተገኘ ሥልጣናቸውን ለመልቀቅ ፈቃደኛ እንደሆኑ ፕሬዚደንት ባርሃም ሳለህ ተናግረዋል- አዲሱ የምርጫ ሕግ መረቀቁን በመግለፅ።

ይሁን እንጂ ተቃዋሚዎቹ አጠቃላይ የፖለቲካ ሥርዓቱ እንዲጠፋ ነው የሚፈልጉት።

በትናንትናው ዕለትም በርካታ ሰዎች " ካርባላ ነፃ ትውጣ! ፣ ኢራን ለቃ ትውጣ! " የሚል ድምፅ ከኢራን ቆንስላ አቅራቢያ አሰምተዋል።

አንዳንድ ተቃዋሚዎች በቆንስላው የግንብ አጥር ላይ ድንጋይ ሲወረውሩና ተቀጣጣይ ነገሮችን ሲያቃጥሉ ተስተውለዋል። ከተቃዋሚዎቹ መካከል ሦስት ግለሰቦችም በአጥሩ ላይ በመንጠላጠል የኢራቅን ሰንደቅ ዓላማ አውለብልበዋል።

ተቃዋሚዎቹን ለመበተን የፀጥታ ኃይሎች እንደተኮሱና በርካታ ሰዎች እንደተመቱ የኤ ኤፍ ፒ የዜና ወኪል ዘጋቢ በሥፍራው ተገኝቸ ታዝቤያለሁ ብሏል።

የዜና ወኪሉ የጤና ባለሥልጣናትን ጠቅሶ እንዳለውም ሦስት ሰዎች ባጋጠማቸው ጉዳት ሕይወታቸው ሊያልፍ ችሏል።

የኢራቅ የሰብዓዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽን ከቆንስላው ግቢ ውጭ በነበረው ግጭት ሦስት ሰዎች መገደላቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል።

ቢቢሲ ከካርባላ ባገኘው የዜና ምንጭ ከሟቾቹ መካከል አንዱ አልፎ ሂያጅ ነው፤ ተኩሱን ማን እንደከፈተ ያልታወቀ ሲሆን የፀጥታ ኃይሎችና ተቃዋሚዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደነበር ገልጿል።

በኢራቅ በያዝነው ወር መጀመሪያ አካባቢ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ እስካሁን ከ250 በላይ ዜጎች ሲሞቱ በርካቶች ደግሞ ለጉዳት ተዳርገዋል።