የአፍሪካ ሕብረት የአፍሪካ ምርጥ መምህራንን ሸለመ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ታትሟል
የአፍሪካ ሕብረት በክፍል ውስጥ የመማር ማስተማር ሂደት አስገራሚ ብቃት ያሳዩ ሦስት የአፍሪካ ምርጥ መምህራንን ሸለመ። የሽልማት ሥነ ሥርዓቱ በአፍሪካ ሕብረት ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ ነበር የተካሄደው።
ለእያንዳንዳቸውም የ10 ሺህ ዶላር [290 ሺህ ብር] የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
መምህራኑ፤ ከጋና አውጉስታ ላርቴይ፣ ከኬንያ ኤሪክ አድምባ፣ እና ከኡጋንዳ ግላዲየስ ኬ ሲሆኑ የተበረከተላቸውን ሽልማት በአካል በመገኘት ተቀብለዋል።
የአፍሪካ ሕብረት ሽልማት ሲያበረክትም ይህ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።
የአፍሪካ ሕብረት የትምህርት ክፍል ኃላፊ ቢያትሪስ ኒጀንጋ "በአፍሪካ ያለውን የመማር ማስተማር ሂደት ለማሳደግ ለምናደርገው ጥረት ጥሩ መነቃቃትን ይፈጥራል" ብለዋል።
ተሸላሚው ኬንያዊው መምህር ኤሪክ በበኩሉ ሽልማቱን በአፍሪካ ያለውን የማስተማር ገፅታ ይለውጣል፤ መምህራንም አዲስ ነገር ፈጣሪ እንዲሆኑ ያበረታታል ሲል ስለተበረከተለት ሽልማት ለጋዜጠኞች አስተያየቱን ሰጥቷል።














