ጥቁር አሜሪካዊቷ በፖሊስ በተተኮሰ ጥይት መኝታ ክፍሏ ውስጥ ተገደለች

የፎቶው ባለመብት, Fort Worth Police Department
በአሜሪካ አንዲት ጥቁር ሴት በመኝታ ክፍሏ መስኮት በኩል በፖሊስ በተተኮሰ ጥይት በትናንትናው ዕለት ህይወቷ አልፏል።
የ28 አመቷ አታቲያና ጀፈርሰን ፎርት ወርዝ በሚባል የመኖሪያ ቦታ ከወንድሟ ልጅ ጋር ትኖር ነበር ተብሏል።
ጎረቤቷ የቤቷ በር መከፈቱን በማየት ደህንነቷን ለማረጋገጥ ይችሉ ዘንድ ወደ ፖሊስ መደወላቸውን አሳውቀዋል።
ፖሊስ ሁኔታውን ያሳያል ብሎ የለቀቀው ቪዲዮ ለሰኮንዶች የቆየን እሰጣገባን ያሳያል።
ቪዲዮው እንደሚያሳየው ፖሊሶች የመኖሪያ ቦታዋን ሲዞሩ የሚታይ ሲሆን በመስኮት በኩል ሰው ሲያዩ እጅ ወደላይ በማለት ከጮሁ በኋላ፤ አንደኛው ፖሊስ በመስኮቱ መስታወት በኩል ተኩሷል።
የፎርት ወርዝ ፖሊስ ኃላፊ በመግለጫቸው ላይ እንዳሉት ነጩ ፖሊስ "አደጋ ላይ እንዳለ ተሰምቶት" ነው የተኮሰው ብሏል።
ምርመራው እስኪጠናቀቅም ድረስ ፖሊሱ ከስራው ለጊዜው መታገዱን ባለስልጣናቱ አስታውቀዋል።

የፎቶው ባለመብት, Facebook
ምንም እንኳን ቪዲዮው ኤዲት ቢደረግም በመስኮቷ በኩል ሲጠጉ ፖሊሶቹ ማንነታቸውን አልተናገሩም።
ከዚህም በተጨማሪም ፖሊስ በመኝታ ክፍሏ ውስጥ መሳሪያ አይተናል ቢሉም በቪዲዮው ላይ የሚታይ ነገር የለም።
በሰዓቱም ግለሰቧ መሳሪያ ስለመያዝ አለመያዟ ፖሊስ ምንም ያላለ ሲሆን፤ በቴክሳስ ህግ መሰረት ከ18 አመት በላይ ያሉ ግለሰቦች መሳሪያ የመያዝ ፍቃድ አላቸው።
ፖሊስ አክሎም ከተተኮሰባት በኋላ ድንገተኛ እርዳታ ሊያደርጉላትም ቢሞክሩም ወዲያው ህይወቷ ማለፉ ተገልጿል።
ቪዲዮ ጌም ስትጫወት ነበር
በወቅቱ ከወንድሟ ልጅ ጋር ቪዲዮ ጌም ስትጫወት የነበረችው ሟች ከቤቷ ውጭ ድምፅ ስትሰማ ጉዳዩን ለማጣራት ወደ መስኮቱ ቀረብ እንዳለች የቤተሰቧ ጠበቃ ተናግረዋል።
"እናቷ ታመው ቤት ውለዋል፤ እናም እሳቸውን ለመንከባከብና ቤቱንም ለመቆጣጠር ነበር የመጣችው፤ ህይወቷን በጣም የምትወድ ሰው ነበረች" በማለት ጠበቃ ሊ ሜሪት በፌስቡክ ገፃችው አስፍረዋል "ለመገደሏ ምንም ምክንያት የለም፤ ምንም፤ ፍትህን እንሻለን" ብለዋል።
ሟቿ የዩኒቨርስቲ ምሩቅ ስትሆን የፋርማሲ ዕቃዎችን በመሸጥ ትተዳደር ነበር ተብሏል።
በቅርቡም አንዲት ፖሊስ ቦታን ጂን የተባለ ጥቁር አሜሪካዊ መኖሪያ ቤት ውስጥ ገብታ ተኩሳ በመግደሏ ፍርድ ቤት የአስር አመት እስር ፈርዶባታል።

የፎቶው ባለመብት, Fort Worth Police Department
በቴክሳስ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ዕጩ ፕሬዚዳንት ቤቶ ኦ ሮውርክ የቴክሳሱን ግድያ ተቃውመው ተናግረዋል።
"በአታቲያና ሞት የተሰማንን ሃዘን እየገለፅን ለሞቷ ኃላፊነት መውሰድ ያለባቸው አካላትን ልንጠይቅ ይገባል። ማንኛውም ቤተሰብ እንዲህ አይነት ሃዘን ላይ እንዳይወድቁ ቃል በመግባት ልንሰራ ይገባል" በማለት በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል።
ለጥቁሮች ነፃነት የሚታገለው ኤንኤንኤሲፒ የተባለው ድርጅት ሞቷን "ተቀባይነት የሌለው" ብሎታል።
የ62 አመቱ ጎረቤቷ ጄምስ ስሚዝ ለፖሊስ ከመደወላቸው በፊት አካባቢውን ተዘዋውረው እንዳዩና ምንም አይነት እንቅስቃሴ ባለማየታቸው ለፖሊስ እንደደወሉ አስረድተዋል።
"በቃላት መግለፅ ከምችለው በላይ ተናድጃለሁ፤ አዝኛለሁ፤ እየተንቀጠቀጥኩም ነው" በማለት የተናገሩት ስሚዝ ደህንነቷን ለማረጋገጥ ለፖሊስ መደወላቸው ፀፀት ውስጥ እንደከተታቸው አስረድተዋል።
"ለፖሊስ ባልደውል እስካሁን በህይወት ትቆይ ነበር" ብለዋል።












