ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኡጋንዳዊው የ2019 የቢቢሲ ኮምላ ዱሞር ሽልማትን አሸነፈ
ኡጋንዳዊው የምርመራ ዘጋቢና የዜና አንባቢው ሶሎሞን ሰርዋንጃ በቢቢሲ ወርልድ ኒውስ የ 2019 ኩምላ ዱሞር ሽልማት አሸናፊ ሆነ።
ሶሎሞን በዩጋንዳ ታዋቂ በሆነው 'ኤንቢኤስ ቲቪ' አቅራቢ ሲሆን በጣቢያው አበይት ጉዳዮችን የሚያቀርብበት ዝግጅት ደግሞ ይበልጥ ታዋቂ አድርጎታል።
ከዚህ በተጨማሪ 'ከቢቢሲ አፍሪካ አይ' ጋር በመተባበር በዩጋንዳ በህገወጥ መንገድ ስለሚሸጡ መድሃኒቶች በሰራው የምርመራ ጥንቅር እስከ መሸለም ደርሷል።
ይህ ሽልማት የተጀመረው ከአምስት ዓመት በፊት በ41 ዓመቱ በድንገት ህይወቱ ያለፈውን ባለድንቅ ችሎታው ጋናዊ የቢቢሲ ጋዜጠኛ ኮምላ ዱሞርን ለማስታወስ ነው።
ከአፍሪካ አዲስ የሚወጡ ባለሙያዎችን ለማግኘትና ለማስተዋወቅ ዓላማን ላነገበው ለዚህ ሽልማት አህጉሪቱ ውስጥ ያሉ ጋዜጠኞች እንዲያመለክቱ ተጋብዘው ነበር።
የዘንድሮው አሸናፊ ኡጋንዳዊው ሶሎሞን ሰርዋንጃ ሽልማቱ ከተጀመረ አምስተኛው ሲሆን ከእሱ በፊት ኬንያዊው ዋይሂጋ ምዋራ በ2015 የተዘጋጀው የመጀመሪያውን ሽልማት ዩጋንዳዊቷ ናንሲ ካቹንጊራ፤ በተከታዮቹ ሁለት ዓመታት ደግሞ ናይጄሪያውያኑ ዲዲ አኪንዬሉሬ እና አሚና ዩጉዳ አሸናፊ ሆነዋል።
ሶሎሞን ከዚህ በመቀጠል ለንደን በሚገኘው የቢቢሲ ዋና መስሪያ ቤት ለሦስት ወራት በመቆት ልምድና ክህሎትን እንዲያገኝ እድል ይሰጠዋል።
ጋዜጠኛው በሃገሩ በደንብ የታወቀና ለጋዜጠኝነት ያለውን ፍቅር በተግባር ማሳየት የቻለ ነው። በኡጋንዳም ለውጥ ያመጡ ብዙ ዘገባዎችን በመስራት ይታወቃል።
'' ኮምላ ስለ አፍሪካ ብዙ ዘግቧል። ነገሮችን ሁሌም ቢሆን በተለየ መንገድ ማቅረብ የሚችል የተዋጣለት ጋዜጠኛ ነበር፤ እሱ የሰራቸው ዘገባዎች በሙሉ አብረውኝ አሉ። እኔም በጋዜጠኝነት አፍሪካውያንን በማገልገል የእሱን በጎ ስም ማስቀጠል እፈልጋለሁ።'' ብሏል ሶሎሞን።
የቢቢሲ ወርልድ ሰርቪስ ዋና ዳይሬክተር ጄሚ አንገስ በበኩላቸው '' በኩምላ ዱሞር ስም ጠንካራ የጋዜጠኝነት ክህሎትን፣ ድንቅ የአቀራረብ ብቃትንና አፍሪካዊ ታሪኮችን በተለየ ሁኔታ የመንገር ችሎታን አጣምረው የያዙ ጋዜጠኞችን ማበረታታት ለእኛ በጣም ጠቃሚ ነው።'' ብሏል።
ለንደን ውስጥ ከቢቢሲ ጋር ከሚኖረው ቆይታ በተጨማሪ ወደ ተለያዩ አፍሪካ ሃገራት በመጓዝ ዘገባዎችን እንዲሰራ ዕድሉን የሚያገኝ ሲሆን ሥራውም በአፍሪካና በዓለም ዙሪያ እንዲቀርብ ይደረጋል።